ኢትዮጵያዊው ወጣት ከንክኪ ነጻ የሆነ የእጅ መታጠቢያ ሰርቶ ለአገልግሎት አዘጋጀ

77

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2012 (ኢዜአ) አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት የፈጠራ ባለሙያ ከንክኪ ነጻ የሆነ የእጅ መታጠቢያ ሰርቶ ለአገልግሎት ዝግጁ አደረገ። 

የፈጠራ ባለሙያው ወጣት ብሩክ ግርማ የዓላማችን ብሎም የአገራችን ስጋት የሆነውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመግታት አንድ አማራጭ የሆነውን የዕጅ መታጠብ ተግባር ከእጅ ንክኪ ነጻ ያደረገ የፈጠራ ሥራውን ይፋ አድርጓል።

የበሽታውን መዛመት ለመግታት ህብረተሰቡ እጁን በውሃ እየታጠበ ቢሆንም የሚታጠብበት መንገድ የሰዎችን የእጅ ንክኪ የሚያበረታታ ብቻ ሳይሆን ውሃን የሚያባክን መሆኑን መታዘቡን ወጣቱ ይገልጻል።

በመሆኑም ከሳሙና መርጨት ጀምሮ ምንም አይነት የእጅ ንክኪ ሳይኖር በእግር በመርገጥ ብቻ መታጠብ የሚያስችልና የውሃ ብክነትንም የሚያስቀር የፈጠራ ውጤት ሰርቷል።

ፈጠራው ለአካል ጉዳተኞም ምቹ ተደርጎ የተሰራ መሆኑን ወጣት ብሩክ ገልጿል።

የፈጠራ ውጤቱን በራሱ ፈቃድ በአሁኑ ወቅት ለምኒልክ ሆስፒታልና ለልደታ ክፍለ ከተማ ፓሊስ መመሪያ ማበርከቱንም ነው የተናገረው።

በቀጣይ ለጥቁር አንበሳና ለጋንዲ ሆስፒታሎችም እንደሚያደርስ አስታውቋል።

"ለአቅመ ደካሞች፣ ለአረጋዊያን እንዲሁም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ የቻልኩትን ያህል ሰርቼ ለማበርከት ተዘጋጅቺያለሁ" ብሏል ።

"በዚህ አስከፊ ወቅት ለወገን ያልሆነ ገንዝብና እውቅት ለማንም አይጠቅምም" ያለው የፈጠራ ባለሙያው፤ ሌሎች መሰል የፈጠራ ባለሙያዎች ያላቸውን ችሎታ፣ እውቀትና ገንዝብ ተጠቅመው ከወገናቸው ጎን ሊቆሙ እንደሚገባም ገልጿል።

የእርሱን የፈጠራ ውጤት በማየትም ሌሎች የፈጠራ ውጤት ባለሙያዎች በቀላሉ የሚገኙ ቁሳቁሶችን በመጠቀም መስራትና በተመጣጠኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ማዳረስ እንዳለባቸው መክሯል።

በአፍሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ1 ሺህ በላይ ሲደርስ በኢትዮጵያም እስካሁን 16 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

የኮሮናቫይረስ በዓለም ላይ እስካሁን 531 ሺህ ሰዎችን ሲይዝ 24 ሺህ ሰዎችንም ገድሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም