ከዓለም እኩል ለመጓዝ ለቴክኖሎጂ ትኩረት መስጠት ይገባል ተባለ

59
አዲስ አበባ ሰኔ 23/ 2010 ከዓለም እኩል ለመጓዝ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ። ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ያስተናገደችው ዓለም አቀፍ የአይሲቲ ኤክስፖ ''በአይሲቲ ኢትዮጵያን ማሸጋገር'' በሚል መሪ ቃል በሚሌኒየም አዳራሽ ተከፍቷል። በመክፈቻ መርሃ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዲጂታል ቴክኖሎጂ ከፍተኛ የተወዳዳሪነት መሳሪያ መሆኑን ገልፀው በውድድሩ ከዘርፉ መሪዎች ጋር አብሮ መሄድ ካልተቻለ ልዩነቶች እየሰፉ እንደሚሄዱ ተናግረዋል። የተጀመሩ የመልማትና የማደግ ስራዎችም በአይሲቲ ተደግፈው ውጤት ማምጣት እንዲችሉ ዘርፉ ላይ በስፋት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል። ''ግብርናችን፣ ኢንዱስትሪያችን፣ ንግዳችን በአጠቃላይ አኗኗራችን በቴክኖሎጂ የሚዘምኑ መሆን አለባቸው'' ነው ያሉት። ቴክኖሎጂና ፈጠራን የመድፈር ተግባርም በሁሉም እንደፋሽን ሊያዝ እንደሚገባም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት። የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ኡባህ መሐመድ በበኩላቸው በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከዓለም ጋር ለመቀላቀል በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጪ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያውያን ወጣቶች የተለያዩ የፈጠራ ግኝቶች እየወጡ እንዳሉ በመናገር ዘርፉ መደገፍ አለበት ብለዋል። በየዓመቱ ከ170 ሺህ በላይ ወጣቶች ከከፍተኛ ተቋማት ተመርቀው ቢወጡም በዋናነት ያላቸውን እምቅ ኃይልና እውቀት በመጠቀም ፈጠራና ምርምር ማውጣት ላይ የሚሰራው ስራ አናሳ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ናቸው። በአሁኑ ወቅት 25 ለምርት መዋል የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች የተለዩ ሲሆን ከነዚህ ወስጥ ለተመረጡ አምስት ፈጠራዎች ዛሬ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዘንድሮው መርሃ-ግብር ላይ የሳዑዲ አረቢያ ዜግነት ያገኘችው ሮቦት ሶፊያ መገኘቷ ኤክስፖው ድምቀት እንዲኖረው ያደርጋል ብለዋል። የሮቦቷ አጠቃላይ ስራ ላይ ኢትዮጵያውያን ከ60 በመቶ በላይ አስተዋፅኦ እንዳለው ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ላለፉት ዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት አይሲቲ ኤክስፖ ያዘጋጀች ሲሆን አለማቀፋዊ ኤክስፖ ስታዘጋጅ ግን ይህ ሁለተኛዋ ነው። ከ100 በላይ ተቋማት ምርቶቻቸውን የሚያሳዩበት ኤክስፖው ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከ200 ሺህ ህዝብ በላይ ይጎበኘዋል ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም