ከውጭ ለሚገቡ መንገደኞች ለ14 ቀናት ማረፊያ የሚያገለገሉ ተጨማሪ ሆቴሎች ተለዩ

65

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2012(ኢዜአ) ከውጭ ለሚገቡ መንገደኞች ለ14 ቀናት ማረፊያ የሚያገለገሉ ተጨማሪ ሆቴሎች መለየታቸውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሆቴሎች በድምሩ ከአንድ ሺህ በላይ አልጋ እንደሚያቀርቡ የተገለጸ ሲሆን በጤና ሚኒስቴር ባለሙያዎች ክትትል ይደረግላቸዋል ተብሏል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር ዛሬ በሰጡት መግለጫ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየሰተራ ነው ብለዋል።

በዚህ መሰረትም ከዚህ ቀደም በግዮንና በስካይ ላይት ሆቴሎች ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ከውጭ ለሚገቡ መንገደኞች ማረፊያ 11 ሆቴሎች ተለይተዋል።

በአዲስ አበባ በተመረጡት ሆቴሎች የሚያገለግሉ ሠራተኞች ተገቢው የጤና አጠባበቅ ሥልጠና በጤና ባለሙያዎች መሰልጠናቸውን ተናግረዋል።

ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሁኔታዎችን የሚከታተል የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም የጸጥታ ሁኔታን የሚከታተል የጸጥታ አካል እንደተመደበላቸውም ገልጸዋል።

በቀጣይም ሁኔታዎች እየታዩ ሌሎች ሆቴሎችን የመለየት ሥራ እንደሚሰራና ይህ አይነቱ ተግባር በክልሎች ላይም ተፈጻሚ እንደሚሆን አስረድተዋል።

በሆቴልና መሰል ዘርፎች ላይ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም በተለይም ከውጭ ለሚመጡ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአነስተኛ ዋጋ አገልግሎት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።   

ዘርፉ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በተቋረጠው የሰዎች ዝውውር በእጅጉ መጎዳቱን ጠቁመው አንዳንድ ሥራዎች ግን በቤት መከወን የሚችሉ መሆኑንና ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ የሚገኙ ሌሎች ሆቴሎች ላይም የሚሰሩ ሠራተኞች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችል የጤና ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ ከውጭ የሚመጡትንም ሆነ በአገር ውስጥ የሚገኙትን የውጭ ዜጎች ልክ እንደ ከዚህ ቀደሙ በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማስተናገድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም