በአርሲ ዞን በ157 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

51

አዳማ  መጋቢት 18/2012  (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ምክንያት በማድረግ በግብርና ምርቶችና የፍጆታ እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉና ሰው ሰራሽ የአቅርቦት እጥረት ፈጥረዋል በተባሉ 157 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአርሲ ዞን አስተዳደር ገለጸ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አሊይ ለኢዜአ እንደገለጹት ከሀገራዊ ጉዳይ የግል ጥቅማቸውን ያስቀደሙ ስግብግብ ነጋዴዎች በሽታውን ምክንያት በማድረግ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  ቀውስ እንዲፈጠር ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው እርምጃው ተወስዶባቸዋል ።

መስተዳደሩ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግና ሰው ሰራሽ የአቅርቦት እጥረት እንዲፈጠር ምርቱን  የደበቁ 157 የንግድ ድርጅቶች ላይ ድርጅታቸውን ከማሸግ ጀምሮ  የንግድ ፍቃድ መንጠቅና ለህግ የማቅረብ እርምጃ መውሰዱን ገልጠዋል።

እርምጃ ከተወሰዳባቸው መካከል ዋና ተዋናይ የነበሩት 12 የንግድ ድርጅቶች ፍርድ ቤት መቅረባቸውንም አመልክተዋል።

በተያያዘ መልኩ በአርሲ ዞን ሥር በሚገኙ 25 ወረዳዎችና ሶስት የከተማ መስተዳድሮች ላይ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉት ላይ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አቶ ጀማል አስረድተዋል።

የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በተለይ ማህበራዊ ትስስሮች ሰርግ፣ ለቅሶ ፣ የእድር ስብሰባዎች ፣ በቤተክርስቲያንና በመስጊዶች የሚደረጉ የአምልኮ ሥርዓቶችም እንዲቆሙ አድርገናል ብለዋል።

በተመሳሳይ የእለት ተእለት ህዝባዊ አገልግሎቶች የሚበዙበት መጠጥ ቤቶች፣ የምሽትና ጫት ቤቶች እንዲዘጉ መደረጉን የገለጹት አቶ ጀማል ሆሲፒታሎችና መናኽሪያ አካባቢ የህዝብ መነካካት እንዳይኖር የመቀነስ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለበሽታው ተጋላጭ የሆነ የህዝብ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከገጠር ወደ ከተማ እንዳይደረግ ጉዞ ለማስቆም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ከዞን ጀምሮ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል አቅም ለመፍጠር የሀብት ማሰባሰብ ሥራ እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ የአርሲ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ ሀሰን ሀጅ ናቸው።

ህብረተሰቡ ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ በቅድመ መከላከልና ጥንቃቄ  ላይ በዞኑ በሚገኙ 500 የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ 312 በሚሆኑት ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥና የማስማር ሥራመሰራቱን ጠቅሰዋል።

በተቀሩት 188 የገጠር ቀበሌዎች ላይ የወረዳ አመራሮችና የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዞኑ ከሚገኙ 107 የጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች የተመለመሉ የጤና ባለሙያዎች በበሽታው ላይ በቂ ግንዛቤና እውቀት  እንዲያገኙ ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በእስከ አሁኑ ሂደት ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች 40 ሺህ የፊት መሸፈኛ ጭምብልና የእጅ ጓንት አከፋፍለናል ያሉት ሃላፊው የጤና ተቋማት በውስጥ ገቢያቸው የንፅህና መጠበቂያዎችን እንዲያሟሉ እየተደረገ መሆኑን ገልጠዋል።

በዞኑ ከዱባይና ሳዑዲ አረቢያ የመጡ የበሽታው ምልክት የታየባቸው 10 ሰዎች ተለይተው በህክምና ባለሙያዎች ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ሀሰን የምርመራ ውጤታቸው እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም