ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከ800 በላይ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ተለቀቁ

120

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2012( አዜአ) ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ ከ800 በላይ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ተለቀቁ።

ታራሚዎቹ የተለቀቁት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በማረሚያ ቤቶች ለመከላከል 4 ሺህ 11 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲለቀቁ በወሰነው መሰረት ነው።

በይቅርታ ከተለቀቁት ከ800 በላይ የህግ ታራሚዎች ውስጥ 561፣ ወንዶች 92 የውጭ አገር ዜጎች ሲሆኑ ከ180 በላይ ነፍሰጡርና ከህጸናት ጋር ታስረው የነበሩትን ጨምሮ ሴቶች ታራሚዎች ናቸው።

ወይዘሮ ዘውድነሽ በቀለ በህግ ከተፈረደባቸው 8 አመት ውስጥ የ2 አመት የእስር ቆይታቸውን ጨርሰው ዛሬ ከህጻን ልጃቸው ጋር በይቅርታ ተፈትተዋል።

በማረሚያ ቤት የወለዱትን ልጃቸውን ይዘው ማህበረሰቡን ሲቀላቀሉ የሚጠብቃቸውን አዲስ ህይወት ለመጀመር ጓጉተዋል።

በአለም ላይ ወረርሽኝ ከሆነው የኮሮናቫይረስ በማለፍ የሚጓጉለትን ህይወት ለመኖር እራሳቸውን ከበሽታው ለመከላከል መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

ከውጭ አገር ዜጎች ታራሚዎች መካከል በይቅርታ የተፈቱት ናይጄሪያዊው ማቲያስ ኤኬኔ የኢትዮጵያ መንግስት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ላደረገው ይቅርታ አመስግነዋል።

አቶ ጊዳኔ ሃይሌም በሽታው ከተከሰተ ጀምሮ በማረሚያ ቤቱ የንጽህና መጠበቂያ ግብአቶች አቅርቦትና ስለበሽታው ግንዛቤ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉም በሽታውን ለመከላከል ንጽህናን መጠበቅ፣ ከንክኪ መራቅና ሌሎች የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር እንደሚተገብሩ ገልጸዋል።

በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት የህግ ታራሚዎች ፍትህ ጉዳይ አስተዳደር ዋና ሳጅን ኢብራሂም አህመድ በጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ውሳኔ መሰረት ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ዜጎች መፈታታቸውን ተናግረዋል።

ከነዚህ ውስጥ አንድ ሰው በልዩ ሁኔታ አጠቃላይ 653 ወንድ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ተለቀዋል።

ዛሬ ከተፈቱት መካከል አንዷ የሆነችው ወጣት ምህረት ይስማሽዋ ''በማረሚያ ቤቱ በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖረው የታራሚ ቁጥር ለበሽታው ስርጭት አመቺ ሁኔታ እንዳይፈጥር ሊታሰብበት ይገባል'' ብላለች።

ዋና ሳጅን ኢብራሂም እንደተናገሩት፤ በማረሚያ ቤቱ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የንጽህና መጠበቂያ ግብአቶችን ማቅረብና ስለበሽታው ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ ነው።

ከአኗኗር አንጻር ታራሚዎች በሚኖሩበት መጨናነቅ እንዳይፈጠር  አዲስ ወደ ተሰራው አባ ሳሙኤል ማረሚያ ቤት ለመውሰድ ዝግጅት ማለቁንም ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስ በዓለም ላይ ከተከሰተ ጀምሮ በኢትዮጵያ ስርጭቱን ለመቀነስና ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየቱ ይታወቃል።


በዚህም በመንግስት ከወሰዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች በተለይም ማህበራዊ ርቀትን ለማስጠበቅ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ እንዲሁም 4 ሺህ 11 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲለቀቁ ተወስኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም