ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ግንኙነቷን ማጠናከሯ በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር አስተዋጽኦ አለው - አስተያየት ሰጪዎች

132
አዲስ አበባ ሰኔ23/10/2010 ኢትዮጵያ ከአጎራባች አገሮች ጋር በአዲስ መልክ ግንኙነቷን ማጠናከሯ በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ሚና እንዳለው የዘርፉ ምሁራን አስታወቁ። ምሁራኑ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፤ ግንኙነቱ ለቀጣናው ከሚያመጣው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በተጨማሪ በቀጣናው የነበራትን ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ የሚያሳድግ ነው። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነትና ተቀባይነትም ሊያጎለብት እንደሚችል ነው ያመለከቱት። የወሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን፤ እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ምስራቅ አፍሪካን ወደ አንድ ለማምጣት እየተጎዙበት ያለው መንገድ አጅግ በጣም የሚያስደስት ነው፡፡ ኢትዮጵያ  ከኤርትራ የበለጠ የሚቀራረባት አገር የለም ያሉት ዶክተር አባተ ኢትዮጵያና ከኤርትራ የጀመሩት ግንኙነት ትልቅ አንደምታ ይኖረዋል ብለዋል በፌዴራል መለስ አካዳሚ የፖለቲካ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ዩሃንስ ተካልኝ፤ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ፓን አፍሪካኒዝምን በመምራት ረገድ በምስራቅ አፍሪካ  ያለውን ሰላም በመጠበቅና ባደራዳሪነት ዋነኛ ሚና ስትጫወት የቆየች አገር ናት ይህ ደግሞ አገሪቱ በቀጠናው ምን ያህል ተቀባይነት እንዳላት ያሳያል ብለዋል፡፡ ባጠቃላይ ኢትዮጵያ አሁን የያዘችው ነገር በፊት የነበራትን ሚና የማጠናከርና በአካባቢው ሰላማዊ የሆነ ሁኔታ እንዲፈጠርና በጋራ አፍሪካን አንድ የማድረግ እቅድ  መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከጂቡቲ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኬንያና ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከሯ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላማዊ የሆነ ከባቢ እንዲፈጥርና ያለውን የተፈጥሮ ሃብት በጋራ እንዲጠቀም የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል። በአገሮቹ መካከል የኢንቨስትመንት፣ የንግድ፣ የቱሪዝም፣ የትራንስፖርት ግንኙነቱን ለማፋጠንና በጋራ ለመልማት የሚያስችሉ እድሎችንም ለመፍጠር እንደሚያስችል አብራርተዋል። ምስራቅ አፍሪካን ከፍተኛ እምቅ አብት ያላት አገር ስትሆን የሚደርስባቸውን ጫና ተቋቁመው ባንድ ላይ ተደምረው መስራት ከቻሉ ካደጉት አገራት የደረሱበት መድረስ ይችላሉ ሲሉ በአካባቢው የተጀመረው እንቅስቃሴ ጥሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ዶክተር አባተ ጌታሁን ናቸው "እስካሁን በነበረው ሂደት አንዱን አንዱ ለማፍረስ ጥረት ሲያደርግ ያንዱን ሰላም አንዱ ለማደፍረስ ሲንቀሳቀስ  የነበረበት ሁኔታ እንደነበር ይታወቃል ያሉት  በፌደራል መለስ ዜናዊ አካዳሚ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሃይለየሱስ ታዬ እንደተናገሩት አገራቱ ሰላማቸውን ጠብቀው በጋራ ከሰሩ  ፣ በጋራ ከቆሙ አብረው ማደግ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ ምሁራኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሮቹን ለማቀራረብና አብሮ ለመስራት ያደረጉትን ጥረት አድነቀዋል። ይህም ተጠናክሮ ከቀጠለ እስከ ኢኮኖሚ ውህደት ሊያደርሰ እንደሚችል ነው ምኞታቸውን የገለጹት። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ የስራ ጉብኝት በማድረግ ከአገሮቹ ጋር የተለያዩ ስምምነቶች መፈረሙ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም