ያለአግባብ ለማትረፍ የሚሹ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል...የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

57

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2012( ኢዜአ) ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ለማትረፍ የሚሹ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ። 

በአገሪቷ የምርት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የተለያዩ አማራጮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።     

ሚኒስቴሩ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የምርት እጥረት እንዳያጋጥም ገበያውን ለማረጋጋት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።   

በሚኒስቴሩ የጥራትና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው እንደተናገሩት፤ ወረርሽኙን ተገን በማድረግ የምርት እጥረት እንዲፈጠርና የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር የሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል።   

በሚኒስቴሩ የሚመራው ግብረ ኃይል የክልል ርዕሰ መስተዳደሮችና የጸጥታ አካላትን በአባልነት ያቀፈ ነው።

የኮሮናቫይረስን ወረርሽኝ መከሰትን ተገን በማድረግ በምርት ማሸሽና ዋጋ ማናር ላይ የተሳተፉ የንግድ ተቋማትና ነጋዴዎች ላይ ከማሸግ ጀምሮ እስከ እስራት የሚደርስ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል።  

በዚሁ መሰረት በአዲስ አበባ 1 ሺህ 406 የንግድ ተቋማት የታሸጉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 156 ጉዳያቸው ወደ ሕግ መወሰዱን ጠቅሰዋል።   

''ኦሮሚያ ላይ ከ 1 ሺህ 700 በላይ የንግድ ተቋማት ሲታሸጉ ለ652ቱ ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል'' ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፤ 30 ነጋዴዎች ሲታሰሩ የ5 ኩባንያዎች የንግድ ፈቃድ እንደተሰረዘ ገልጸዋል።  

በተመሳሳይም በደቡብ፣ ትግራይ፣ አማራ፣ ጋምቤላና ሀረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የንግድ ተቋማትን ከማሸግ ጀምሮ እስከ እስር ድረስ የደረሰ እርምጃ በግብረ ኃይሉ መወሰዱን ተናግረዋል።  

ይቅርታ የጠየቁ ንግድ ተቋማት እየተከፈተላቸው ነው ያሉት አቶ እሸቴ፤ በእርምጃው የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በኀብረት ሥራ ዩኒየኖች በኩል ለከተማ እንዲቀርብ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።

እንደ ሚኒስትር ደኤታው ገለጻ፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ያለምንም ችግር በጅቡቲና ሱዳን በኩል እየገቡ ሲሆን 650 ሺህ ኩንታል ስንዴ፣ 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይትና 300 ሺህ ኩንታል ስኳር ከውጭ በየወሩ እየገባ ነው።  

በሚኒስቴሩ የአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ጨርቃጨርቅና ፋርማሲቲካል ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ በበኩላቸው በአገሪቷ ያሉ ኩባንያዎች የሳኒታይዘር፣ ጓንትና የአፍ መሸፈኛ ማስክ እንዲያመርቱ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በተለይ ከሳኒታይዘር ምርት ጋር በተያያዘ የአልኮል እጥረት እንደገጠማቸው ጠቅሰው፤የግብዓት እጥረቱን ለማቃለል ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።  

በዚህም መሰረት 13 አምራቾች ሳኒታይዘር ለማምረት የሚያስፈልጋቸውን 750 ሺህ ሊትር አልኮል ከስኳር ኮርፖሬሽን እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።  

በአሁኑ ወቅት 200 ሺህ ሊትር ሳኒታይዘር ተመርቶ መከፋፈሉን የገለጹት አቶ ተካ፤ ለአረጋዊያን ማቆያ፣ ማረሚያ ቤቶች፣ ለፌዴራል ፖሊስና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ቅድሚያ በመስጠት እንዲቀርብ እየተደገ እንደሆነም ጠቁመዋል።   

የአፍ መሸፈኛ ማስክ የሚያመርቱ ኩባንያዎችም የአቅርቦት እጥረት እንዳይገጥማቸው ድጋፍ እየተደገ እንደሆነም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም