የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ለፍሬ እስኪበቃ ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን

97

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለፍሬ እስከሚበቃ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። 
የግድቡ የመሰረተ ድንጋይ ከተጣለ አንስትቶ አቅም በፈቀደ መልኩ ገቢያቸው በመቀነስ በቦንድ ግዢና በስጦታ መላ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተለያዩ የህብረተስብ ክፍሎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።ግድቡ የኢትዮጵዊያን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ህዝብ በራሱ አቅም፣ ተነሳሽነትና ፍላጎት በርካታ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ድጋፉ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
አቶ ዮናስ ተፈራ ግድቡ ህጻን አዋቂ ሳይባል ሁሉም የተረባረበበት በመሆኑ ግንባታው ውጤታማ እስኪሆን አስተዋጽኦቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ተማሪ ብርሃን በላይ በበኩሉ የአቅሙን የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን የተለያዩ የንቅናቄ መድረኮች ላይ በመሳተፍ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

ቦንድ በመግዛት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ አሰፋ ያለው በበኩላቸው ሁሉም ወገን ለግድቡ ግንባታ ስኬት መተባበር እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት 9ኛ ዓመት መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች የሚከበር ይሆናል።

የስነ-ስርዓቱ አንድ አካል የሆነው የቦንድ ሳምንት ከትናንት በስትያ በይፋ መጀመሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም