የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማጠናከር በትጋት እሰራለን- የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች

58
ሀዋሳ ሰኔ 23/2010 በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማጠናከር በሰለጠኑበት የሙያ መስክ በትጋት እንደሚሰሩ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ከ8ሺህ በላይ ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡ በመልካም አስተዳደር የትምህርት መስክ በመጀመሪያ ዲግሪ በማዕረግ የተመረቀችው ወጣት ቸኮለች ነሲቡ በሰጠችው አስተያየት አካል ጉዳተኝነትና ሴትነት ከባድ ቢሆንም ባደረገችው ጥረት አላማውን ማሳካት እንደቻለች ተናግራለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረው መነሳሳትና ተስፋ ቀጣይ እንዲሆን የሚጠበቅባትን በመወጣት ለለውጥ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች፡፡ በሶስተኛ ዲግሪ መርሀ ግብር በአፕላይድ ሂሳብ የተመረቁት ዶክተር ቢንያም ተፈሪ በበኩላቸው በሀገሪቱ በተጀመረው ለውጥ ውስጥ የራሳቸውን አስተዋጽኦ  ለማበርከት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጎን ለመቆም ቃል ገብተዋል፡፡ "ሀገሪቱ ብዛት የሰው ኃይል ያስፈልጋታል”  ያለው ዶክተር ቢንያም "የተማርኩትን ትምህርት ለሌሎች በማካፈል የሚጠበቅብኝን ለመስራት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሚሊዮን ማትያስ በስነስርዓቱ ወቅት እንዳሉት ተመራቂዎች በአሁኑ ወቅት  በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን የለውጥ ጉዞ ከዳር ለማድረስ  የሚጠበቅባችውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ የዘንድሮ ተመራቂዎች መንግስት ለወጣቶች ልዩ ትኩረት እየሰጠ ባለበትና ሀገሪቱ የዓለምን ትኩረት እየሳበች በአዲስ የለውጥ ሂደት በምትገኝበት ወቅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዛሬ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ ፣ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ መርሀ ግብር 8ሺህ 600 ተማሪዎችን ማስመረቅ እንደቻለና ከነዚህ ውስጥ 29 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አቶ አያኖ በራሶ ናቸው፡፡ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከ53 የውጪና 12 የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተባብሮ እየሰራ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም