ቅዱስ ሲኖዶስ ከመንበረ ፓትሪያርክ እስከ አህጉረ ስብከት ጽህፈት ቤቶች በከፊል እንዲዘጉ ወሰነ

127

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2012 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የመንበረ ፓትሪያርክና መላው አህጉረ ስብከት ጽህፈት ቤቶች በኮሮናቫይረስ ምክንያት በከፊል እንዲዘጉ ወሰነ። ውሳኔው ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም ሲኖዶሱ መወሰኑን ቤተክርስቲያኗ ዛሬ በሰጠችው መግለጫ አስታውቃለች።

ቅዱስ ሲኖዶሱ ዛሬ የወሰነውን ውሳኔ አስመልክቶ በመንበረ ፓትሪያርክ ፅህፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአርሲ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ያሬድ መግለጫ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ በከፍተኛ ፍጥነት የሰው ልጆችን ህይወት በሞት እየቀጠፈ ያለው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

"በዚህ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ወረርሽኙን ለመቋቋም የበኩሏን እንቅስቃሴ እያደረገች ነው" ብለዋል ብፁዕ አቡነ ያሬድ።

ቤተክርስቲያኗ ካለባት ህዝባዊ ኃላፊነት የተነሳ ቫይረሱን ለመከላከል ራሱን የቻለ የተስፋ ግብረኃይል በማቋቋም ህብረተሰቡ ከበሽታው እንዲጠበቅ እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይ ከቫይረሱ ራስን በተገቢው መንገድ መጠበቅ እንዲቻል ቋሚ ሲኖዶሱ ዛሬ ስብሰባ አድርጎ በሰፊው በመነጋገር በጊዜያዊነት መዘጋት የሚገባቸው የሥራ ክፍሎች ላይ ውሳኔ ማሳለፉን አመልክተዋል።

በዚሁ መሰረት ቅዱስ ሲኖዶስ ከመንበረ ፓትሪያርክ እስከ አህጉረ ስብከት ጽህፈት ቤቶች በከፊል እንዲዘጉ መወሰኑን ጠቁመዋል።

"በጠቅላይ ቤተክህነትና በቤተክህነቱ ስር ከአዲስ አበባ እስከ አህጉረ ስብከት ያሉ የሥራ ክፍሎች በጊዜያዊነት እንዲዘጉ ተደርጓል" ብለዋል ።

ብፁዕ አቡነ ያሬድ እንዳሉት ቤተክርስቲያኒቷ ዶግማና ቀኖናዋን በማይነካ መልኩ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ መመሪያዎችን አስተላልፋ ተግባራዊ እያደረገች ነው።

የተቋቋመው ግብረኃይልም ከጠቅላይ ቤተክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት መዋቅሩ መመሪያ አውርዶ ተፈጻሚ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም