በአፋር ክልል ኮሮናን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የኃይማኖት አባቶች እንዲያግዙ ተጠየቀ

70

ሰመራ  መጋቢት 16/2012 (ኢዜአ) በአፋር ክልል ኮሮናን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት የኃይማኖት አባቶች በማገዝ የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በበሽታው መከላከል ዙሪያ ከኃይማኖት አባቶች ጋር ዛሬ በሰመራ ከተማ መክረዋል።

በምክክሩ መድረክ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት የክልሉ መንግሰት  በሽታውን ለመከላከል  ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው።

ለዚህም  በጀት መመደቡንና  የተለያዩ አደረጃጀቶች እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ መዋቀራቸውን  ተናግረዋል።

ህብረተሰቡን ከንክኪ ታቅቦ የራሱንና ቤተሰቡን ጤና በመጠበቅ በሽታውን እንዲከላከል  በተለይ የኃይማኖት አባቶች  ያላቸውን  መዋቅር ተጠቅመው በማስተማር  የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ወጣቶችም   የበጎ-ፍቃድ አገልግሎት ስራ ላይ በንቃት በመሳተፍ  እንዲያግዙም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የክልሉ  ጤና ቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ በበኩላቸው  ለጅቡቲ በሚቀርበው ጋላፊ ጉምሩክ ኬላ እስካሁን ከ53ሺ በላይ ሰዎች ተመርምረው  ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆነ ተጠርጣሪዎች አለመገኘታቸውን አስታውቀዋል።

በሰመራ ከተማ  የለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲሁም በሽታው ቢከሰት እንኳን የዱብቲው ጨምሮ በአምስት ሆስፒታሎች የህክምና  መሰጪያ ክፍሎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው የኃይማኖት  መላከ-ሰላም አባመአዛ መልኬ በሰጡት አስተያየት ምዕመናኑ የሃኪምን ምክር  በአግባቡ ተግባራዊ እንዲያደርግ በማስተማር በሽታውን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ሸሪአ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ መሃመድ ደርሳ በበኩላቸው በሽታውን ለመከላከል  ከሌሎች ባለድርሻ አካላትጋር በመሆን እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም