የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናቸውን አንድ ሺህ 87 ተማሪዎች አስመረቀ

51
ጋምቤላ ሰኔ 23/2010 የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ  ለአራተኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን አንድ ሺህ 87 ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ ዛሬ አስመረቀ። የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ወቅት እንደገለጹት ያስመረቋቸው ተማሪዎች በመደበኛና በተከታታይ የትምህርት መረሃ ግብር በ17 የሙያ ዘርፎች ነው። ከተመራቂዎቹ መካከል 31 በመቶ ሴቶች ናቸው። ተመራቂዎቹ ከሰለጠኑባቸው የሙያ ዘርፎች መካከል ግብርና፣ ተፈጥሮ ሃብት፣ እንስሳት ሳይንስ፣ ምጣኔ ሀብት፣ እጽዋት ሳይንስና  ሰው ሀብት አስተዳደር ይገኙበታል። እንደ ዶክተር ኡጁሉ  ገለፃ የዩኒቨርሲቲው ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ተማሪዎች የተሻለ እወቀት ይዘው እንዲወጡ እየሰራ ነው። በቀጣይም በእውቀትና በስነ- ምግባር የተገነባ ዜጋ በማፍራትና ችግር ፊች የምርምር ስራዎችን በማከናወን በሀገሪቱ ለታለሙት የልማት ግቦች ስኬት የድርሻውን ለመወጣት እንደሚሰራ ተናግረዋል የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሰናይ አኩዎር እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን በማከናወን የተጀመረውን ልማት መደገፍ ይኖርበታል። በተለይም በእውቀት፣ በመልካም ስነ- ምግባር የታነጸና ሀገራዊ አመለካከት ያለው ዜጋ  በማፍራትና የማህበረሰቡን ህይወት የሚለውጡ የምርምር ስራዎችን በማከናወን ረገድ ዩኒቨርሲቲው በትኩት መስራት ይጠበቅበታል። ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ልምድ በመጠቀም ሀገሪቱን ወደ ቀድሞው ታለቅነቷ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አቶ ሰናይ አሳሰበዋል። በትምህርቱ አጠቃለይ ብልጫ በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ተማሪ በርሄ አፈራ በሰጠው አስተያየት  በሰለጠነበት የሙያ ዘርፍ ህብረተሰቡን በቅንነትና በተማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን ለውጥ ከብሄርተኝነትና ከጎሰኝነት አመለካከት በጸዳ ለማገልገል እንደምትስራ የገለጸችው ደግሞ ሌላዋ ተመራቂ  ስመኝ ወንድም ናት። የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የዛሬዎቹን ጨምሮ እስካሁን ሶስት ሺህ የሚጠጉ ባለሙያዎችን ማስመረቁ  በስነስርዓቱ ላይ ወቅት ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም