ኦሮሚያ በቦንድ ሽያጭ ሳምንት 150 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዘመቻ ጀመረ

76

አዳማ መጋቢት 16/2012 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል በቦንድ ሽያጭ ሳምንት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 150 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ዘመቻ መጀመሩን የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የክልሉ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዴረሳ ተረፈ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የግድቡ ግንባታ የተጀመረበትን ዘጠነኛ ዓመት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት መጀመሩን ገልጸዋል።

በዚህም 150 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት በክልሉ 22 ዞኖችና 344 ወረዳዎች ህዝባዊ ንቅናቄና የቦንድ ሽያጭ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ከመጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት በልማት ባንክና በንግድ ባንክ የቦንድ ሽያጭ የሚካሄድ መሆኑን የገለጹት አቶ ዴሬሳ ለእቅዱ ውጤታማነት በየደረጀው አደረጃጀት በመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በክልሉ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከ1 ቢሊዮን 850 ሚሊዮን ብር በላይ  በስጦታና በቦንድ ግዥ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ህብረተሰቡ በገንዘቡ፣ በእውቀቱ፣ በጉልበቱና  በሞራል  የሚያደርገውን ድጋፍና ተሳትፎ  ወሳኝ መሆኑን የገለጹት አቶ ዴሬሳ  ይህን  ለማሳካትም  ርብርቡ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም