የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑ አስታወቀ

101

 አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15፣ 2012 የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን መጀመሩን አስታወቀ። 

ድርጅቱ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በድርጅቱ የእርድ አገልግሎትና ስርጭት ዳይሬክተር አቶ ሸዋለፋ ይትባረክ በመግለጫው እንዳሉት ስለኮሮናቫይረስ የተቋሙ ሠራተኞች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል።


በአሁኑ ወቅት ሠራተኞቹ ወደ እርድ ክፍል ሲገቡ ንጽህናቸውን የሚጠብቁበትን የእግር መንከሪያ ወይም ‘ፉት ባዝ’ አገልግሎት እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው።

መጪውን የፋሲካ በዓል ተከትሎ በእንስሳት እርድ ላይ የሚፈጠርን መጨናነቅ ለመቀነስ ተጨማሪ የእርድ ክፍሎች ግንባታና እድሳት ሥራዎች ከፋሲካ በዓል በፊት በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ሲሆን ቫይረሱን ለመከላከል የተቋቋመ ኮሚቴ መኖሩንም ጠቁመዋል።

ለዚህም ድርጅቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መመደቡን ነው ያስታወቁት።

“የእርድ ክፍሎችንና የሥጋ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎችን ለትንሳኤ በዓል ዝግጁ ለማድረግ የመኪኖቹን ግድግዳና ብረቶችን የመቀባት ሥራ እየተከናወነ ነው” ብለዋል።

በድርጅቱ የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት ባለሙያ አቶ ማቴዎስ ግርማ በበኩላቸው የእርድ ከብቶች ምርመራ የተለመደ ቢሆንም ከወትሮው በተለየ የድርጅቱ ሠራተኞች ከኮሮናቫይረስ ምንያህል ተጠብቀዋል? የሚለው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
“ለዚህም በአሁን ወቅት የሥጋ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎችን ከቫይረሱ ነጻ ለማድረግ ከውሃ በተጨማሪ ኬሚካሎችን እየተጠቀምን ነው” ብለዋል።
ድርጅቱ የጤና ሚኒስቴር የሚያሰራጨውን መረጃ እየተከታተለ የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጣ ገልጸዋል።
በድርጅቱ መግቢያና መውጫ በሮች ላይ ለሠራተኞቹና ለደንበኞቹ በሳሙናና ሳኒታይዘር የታገዘ የእጅ መታጠብ አገልግሎትን ተደራሽ መደረጉንም አመልክተዋል።

ስለበሽታው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው የገለጹት። 


የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በቀን ለ3 ሺህ የእንስሳት እርድ አገልግሎት የመስጠት አቅም ቢኖረውም በአሁኑ ወቅት እያከናወነ ያለው ከ300 እስከ 400 ከብቶችን ብቻ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም