በርበሬን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀየጥ ስትሸጥ የተገኘች ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለች

96

ድሬዳዋ፣ መጋቢት 15/2012 (ኢዜአ) በርበሬን ከተለያዩ ባዕድ ነገሮች ጋር በመቀየጥ ስትሸጥ ተገኝታላች የተባለች ግለሰብ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

በድሬዳዋ የመጋላ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር አብዱልቃድር አክመል እንዳሉት ድርጊቱን የደረሱበት የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ እየተፈጠረ ያለውን የዋጋ ንረት ለመከላከል እየተሰራ ባለበት ወቅት በህብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት  ነው።

ጥቆማውን ተከትሎ ከንግድ ማስተባበሪያ ጋር በተደረገ ፍተሻ ግለሰቧ በወፍጮ ቤቷ ፣ከደቃቅ አፈር ፣ነጭ ሽንኩርት ልጣጭና  ሌላም ባዕድ ነገር ጋር የተለወሰ በርበሬ በመፍጨት ቀይጣ  ለሽያጭ እያቀረበች እያለ ትላንት መያዟን አመልክተዋል።

ከግለሰቧ ሌላ አራት ግብረአበሮቿም  በቁጥጥር ስር ውለው በምርመራ ላይ እንደሚገኙ  ያመለከቱት  ምክትል ኢንስፔክተሩ የህብረተሰቡን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ህገወጥ ግለሰቦችን በመቆጣጠር ለህግ የማቀረቡ ሥራ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪ በርበሬ መፍጫው መጋዘን ውስጥ የተበላሹና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው 14 ኩንታል የዱቄት ወተት በቁጥጥር ስር መዋሉንም ጠቁመዋል፡፡

ህብረተሰቡ ህገወጦችን በመጠቆም እያደረገ ያለውን ትብብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በወፍጮ ቤቱ ላይ የተወሰደውን እርምጃ የተመለከቱት አቶ አቡበከር ሙሳ "ችግሩን በተደጋጋሚ ጊዜ ለቀበሌ አመልክተናል፤ ግን የሚወሰድ እርምጃ አልነበረም"ብለዋል፡፡

አሁን የተወሰደው እርምጃ ቢዘገይም ትክክለኛና ለህብረተሰቡ ጤና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ተመሣሣይ ችግር በቀፊራ ገበያ ውስጥ አለ፤ እርምጃው መጠናከር አለበት" ያሉት ደግሞ አቶ አንተነህ ተስፋዬ ናቸው፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም