መስሪያ ቤቶች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መፍትሔዎችን ሊወስዱ ይገባል

111

መጋቢት15/2012ዓ.ም (ኢዜአ) መስሪያ ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከተቋማቸው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር መፍትሔዎችን መውሰድ እንደሚገባቸው የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አሳሰበ። 
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የስራ ቦታዎች ምቾት የማይፈጥሩና ለንክኪ የሚያጋልጡ ከሆኑ ሠራተኞች ቤታቸው ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሲቪል ሰርቪስ መስሪያ ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ያስቀመጣቸውን አካሄዶች መተግበር ግዴታ ነውም ተብሏል።

ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ ለኢዜአ እንደገለጹትም ሰራተኞች በጤና ሚኒስቴርና በሌሎች አካላት የሚተላለፉ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባቸዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም ከተቋሙ አንፃር ዕድሜያቸው ከ42 ዓመት በላይ የሆኑ፣ ልጆቻቸውን በማቆያ የሚያውሉና የሚታወቅ ሕመም ያለባቸው ሠራተኞች እረፍት እንዲወስዱ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ነገር ግን ተቋማት የሰራተኞቻቸውን ጤና በመጠበቅና በቢሮ ውስጥ የሚኖሩ መጨናነቆችን በመቀነስ ረገድ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ሕዝብ የሚበዛባቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተጨማሪ ቅርንጫፎችን መክፈትና ሰራተኞቻቸው የአንድ ለአንድ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባቸውም ጠቅሰዋል።

አገልግሎት ፈላጊው ሕብረተሰብም በአገር ደረጃ ቫይረሱን መከላከል እስኪቻል አማራጭ ካልጠፋ በቀር ወደ ተቋማቱ መሄዱን ቢቀንስ ሲሉም መክረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የቢሮ አቀማመጥና የትራንስፖርት ሁኔታቸው ምቹ ያልሆኑላቸው ሰራተኞች ቤታቸው ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል ብለዋል።
ለዚህም መስሪያ ቤቶች እንደ ነባራዊ ሁኔታቸው መፍትሔ እንዲያበጁና በተቀመው አግባብ ተግባራዊ እንዲሆንም መግባባት ላይ መደረሱን ነው የገለጹት።

ቫይረሱን ለመከላከል ሁሉም ሰው ርቀቱን ጠብቆ እንዲቀመጥና እንዲንቀሳቀስ የተቀመጠውን መመሪያ መተግበር ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም