በድሬዳዋ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

65

ድሬዳዋ፤ መጋቢት 15/2012 (ኢዜአ)በድሬዳዋ ከተማ 10 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን የድሬዳዋ ጉምሩክ ኮሚሽን ገለፀ ።

ህጋዊ ንግድን የሚያዛቡና ለህብረተሰቡ ጤና ጠንቅ የሆኑትን ተግባራት ለመከላከል በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡

በፈዴራል ጉምሩክ ኮሚሽን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የኮትሮባንድ ክትትል አስተባባሪ አቶ ኤርሚያስ ቦጋለ ለኢዜአ እንደገለፁት የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት በህብረተሰቡን ጥቆማ መሰረት የፌደራልና የድሬዳዋ ፖሊስ በቅንጅት በወሰዱት እርምጃ ነው ።

በድሬዳዋ ልዩ ስሙ ጀርባ በሚባል የብሎኬት ማምረቻ ውስጥ ሥርዓት በሌለው መንገድ ተደርድረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ምግብ ነክ ሸቀጦች መካከል የታሸጉ ዘይቶች በርካታ መሆናቸው ተጠቅሷል።

በተጨማሪም ብዛት ያላቸው የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች ተይዘዋል ።

ከተያዘው ዕቃ ተያያዥነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም አውስተዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር በበኩላቸው ለሀገርና ለህብረተሰቡ ጠንቅ እየሆነ የመጣውን የኮትሮባንድ መረብ ለመበጣጠስና ለማስቀረት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ኮትሮባንድ ህጋዊውን የንግድ እንቅስቃሴ እያዛባና የህብረተሰቡን ጤና ችግር ላይ እየጣለ መሆኑን የተናገሩት ሃላፊው

ችግሩን ለመከላከልና ለማስቀረት በተናበበና በተቀናጀ መንገድ የመከላከሉን ስራ ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡም በህገ-ወጥ መንገድ የሚቀርቡለትን ሸቀጦች ባለመጠቀምና ችግሩን በመከላከል ሀገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም አቶ አብዲ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም