የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ ሣምንት ተጀመረ

146

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15/ 2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ ሣምንት ከዛሬ ጀምሮ በይፋ መጀመሩን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የቦንድ ሽያጩ የሚካሄደው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በኢትዮጵያ ልማት ባንክና በገጠር ባሉ አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ነው።

የቦንድ ሽያጩ ለአንድ ሣምንት እንደሚቆይ የተነገረ ሲሆን “ጤናችን ይጠበቃል  ግድባችን ይጠናቀቃል” በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ  ላይ እንዳሉት፤ የቦንድ ሽያጭ ሣምንት ይፋ የተደረገው ግድቡ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበትን ዘጠነኛ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡

የግድቡ ግንባታ አሁን ያለበት 71 በመቶ ላይ እንዲደርስ በአገር ውስጥና በውጪ አገር  የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ሲያደረጉ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ለዚህም እስከ አሁን ድረስ 13 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንም አስታውቀዋል፡፡

''ኢትዮጵያ ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት እንዲኖር እየሰራች ነው'' ያሉት ወይዘሮ ሮማን፤ ይህን ሃቅ አንቀበልም ያሉ አገሮች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

''ይሁንና በኢትዮጵያ በኩል አሁንም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን በሙሉ ልብ እየተሰራ ይገኛል'' ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገር መሆኗን የገለጹት ወይዘሮ ሮማን አሁንም  ይህን ጠብቃ የኖረችውን ሉአላዊነት ለማንም አሳልፋ አትሰጥም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ቦንድ ሽያጭ ሳምንትም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ህዝቦች ጠንካራ  ተሣትፎ እንዲያደረጉ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሃይለየሱስ በቀለ በበኩላቸው ''በልማት ባንክ ከዚህ ቀደም እንደተደረገው ሁሉ የቦንድ ህትመትና ሽያጭ ይከናወናል'' ብለዋል፡፡

ለዚህም ለቦንድ ሽያጭ ሣምንቱ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ የቦንድ ሽያጭ ሣምንት ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ላይ የዋሌት ሙሉ ጥላዬ ኢንትርናሽል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር  ዳይሬክተር ወይዘሮ ትህትና ለገሠ አንድ ሚሊዮን ብር ስጦታ አበርክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሄራዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ቦንድ በስጦታ ለሚያበረክቱ 1000291929609 እንዲሁም የቦንድ ግዢ ለሚፈጽሙ 1000291927738 የባንክ ሂሳብ ቁጥር መክፈቱ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ህዝቦች ተሣትፎ እየተገነባ የሚገኘው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበት ዘጠነኛ ዓመት መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም