የኮሮናቫይረስ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ጫና መቀነስ የሚያስችል ምክረ ሀሳብ ቀረበ

44

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ጫና መቀነስ የሚያስችል የድጋፍ ምክረ ሀሳብ ለቡድን 20 አባል ሀገራት አቀረበች።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዛሬ ባወጣው የድጋፍ ምክረ ሃሳብ ላይ የቫይረሱ ስርጭት የሚያስከትለውን ጫና በዝርዝር አስረድቷል።

ኮሮናቫይረስ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል የሚለው ምክረ ሀሳቡ፤ የሚያስከትለውን ሥጋት በዝርዝር ጠቁሟል።

በዓለም ደረጃ የወጪ ንግድ መጠን መቀነስ፣ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች መላላት እና የጉዞ እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ክፉኛ መጎዳት እንደሚያስከትልም አመልክቷል።

ጫናውንም ከኢትዮጵያን አንፃር ሲገልጽም፤ የሀገሪቱን ወጪ ንግድ ሁለት ሶስተኛውን ገቢ የሚያመጣው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በገጠመው የበረራ መዳረሻዎች መቀዛቀዝ በኢኮኖሚዋ ላይ ስጋትን ደቅኗል ብሏል።

ኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚመጣውን ጫና ለመቀነስ ከአጋር ሀገራት ጋር እየሰራች መሆኑን ያመላከተው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የቡድን 20 አባል ሀገራት በቀጣይ በሚያደርጉት ልዩ ስብሰባቸው ከግምት ውስጥ ቢያስገቧቸው ያለችውን ባለ ሶስት ነጥብ ምክረ ሀሳብ ማቅረቧንም ገልጿል።

ከቀረበው ምክረ ሃሳቡ መካከል ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የኮቪድ-19 የአስቸኳይ ጊዜ የፋይናንስ ድጋፍ ማዕቀፍ ይገኝበታል።

ለአስቸኳይ ጊዜ ድጋፉም 150 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግ እና የገንዘብ ድጋፉም የውጭ ምንዛሬ አቅምን እና የሴፍቲ ኔት መርሃ ግብሮችን ለማጠናከር የሚውል መሆኑ ምክረ ሃሳቡ አመልክቷል።

በምክረ ሃሳቡ የተጠቀሰው ሌላኛው ነጥብ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የአስቸኳይ ጊዜ የጤና ማዕቀፍ ነው።

በዚህም ለዓለም ጤና ድርጅት የሚደረገውን ድጋፍ በማጠናከር ሲሆን፤ ድርጅቱ በአፍሪካ የሚያደርገውን ድጋፍ ማሳደግ፤ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል /ሲዲሲ አፍሪካ/ እንዲሁም ለኤች አይቪኤድስ፣ ወባ እና ቲቢ መከላከያ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ድጋፎችን ማጠናከር የሚለውም ነጥብ ተካቷል።
በሶስተኛው የምክረ ሃሳቡ ነጥብ ላይ በአፍሪካ ሀገራት ላይ ያሉ እዳዎች እንዲሰረዙ እና የብድር መመለሻ ጊዜዎች እንዲራዘሙ ጠይቋል።

በዚህም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ላይ ያሉ የብድር ወለዶች እንዲሰረዙ እንዲሁም፤ የመክፈያ ጊዜያቸው የተቃረቡ ብድሮች ደግሞ ቢያንስ ለ10 ዓመታት እንዲራዘሙ ኢትዮጵያ ለሀብታሞቹ ሀገራት ባቀረበችው ምክረ ሃሳብ ጠይቃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም