ኮሮናን በተመለከተ በመቀሌ ገበያ መዘናጋት ሲታይ በማይጨው የተሻለ ነው

65

መቐለ / ማይጨው ኢዜአ መጋቢት15/2012ዓ/ም. በመቐለ ከተማ ብዙ ህዝብ በሚሰበሰብበት የሰኞ ገበያ የማስተካከያ እርምጃ ካልተወሰደ የኮረና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ገበያተኞች ሲገልፁ በማይጨው ገበያ ያለው ጥረት ግን የተሻለ ነው ተባለ ።

በመቐለ ከተማ በየሳምንቱ ሰኞ  የሚቆመውን ታላቅ የህዝብ ገበያ በርካታ ህዝብ ተጠጋግቶና በመነካካት ትናንትም በተለመደው አግባብ ግብይቱ ሲካሔድ ውሏል ።

ከገበያተኞቹ መካከል አቶ ሀይለ አስረስ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶች  በመገናኛ ብዙሀን በርካታ መልእክት ቢተላለፍም ህብረተሰቡ ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግ በኩል ቸልተኝነት እንደሚበዛበት ተናግረዋል ።

በገበያው ሸማቹና ሻጩ እጅግ ተቀራርቦ፣እጅ ለእጅ ገንዘብ እየተቀባበለና ቫይረሱን ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ለማስተላለፍ በተጋለጠ አግባብ መካሔዱ ስጋት እንዳሳደረባቸው አስተያየት ሰጪው ገልፀዋል ።

መንግስት ስለ በሽታው ስርጭት ትምህርት እየሰጠ ቢሆንም መልእክቱን ተቀብሎ ተግባራዊ የሚያደርግ ማህበረስብ አነሰተኛ በመሆኑ የጠቀሱት ደግሞ አቶ ዓሊ አበባው ናቸው።

ማህበረሰቡ አሁን እየተከተለው ያለውን የግብይት ስርአት በሽታው ከሰው ወደ ሰው ለመተላለፍ አመቺ  በመሆኑ ማስተካከያ እንዲደረግ ጠይቀዋል ።

በታክሲ ትራንስፖርት ላይ የሚታየው ተጠጋግቶ መቀመጥ፣ከልክ በላይ ትርፍ መጫንና መስኮት ያለመክፈት ጉዳይም ሊታሰብበት እንደሚገባው ጠቁመዋል።

ችግር ከደረሰ በኋላ ከመራሯጥ ይልቅ ለመከልከል ልዩ ትኩረት መሰጠት አለባት ያሉት ደግሞ አቶ ገብሩ ተላ የተባሉ  የከተማው ነዋሪ  ናቸው

የክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግኑኝነት አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ተስፋይ በበኩላቸው  በገበያ ቀኖችና ህብረተሰቡ በብዛት በሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች  እየታየ ያለውን የህዝብ መጨናነቅና መጠጋጋት ለመገደብ በድምጽ ማጉያ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በመናኽሪያዎችና በታክሲ መነሻና መዳረሻ ቦታዎች  ርቀቱን ጠብቆ ወረፋ እንዲይዝና ከመጨባበጥና ከንክኪ እንዲጠነቀቁ የጤና ባለሙያዎች ትምህርት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በማይጨው ከተማ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ገበያ የሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን እጃቸው በሳሙና እንዲታጠቡና አልኮል እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ተገልጿል ።

በመከላከል ስራው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በየቦታው ውሃ፣ ሳሙናና አልኮል በማቅረብ ድጋፍ እያደረጉ ናቸው ተብሏል ።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት በጣም አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ናቸው ።

ሰብአዊ ድጋፍ መስጠት ከትንሽ ነገር ይጀመራል ያሉት ወጣቶቹ ባላቸው አቅም ድጋፍ እያደረጉና የግንዛቤ ትምህርት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ወጣት ሰሎሞን ከላሊ በሰጠው አስተያየት በማይጨው ከተማ ቅዳሜ ገበያ በሚባል ቦታ በርካታ ህዝብ የሚሰበሰብበት በመሆኑ ቫይረሱ በቀላሉ እንዳይስፋፋ የመከላከል ስራጀምረናል ብሏል።

ወረርሽኙን ለመከላከል ህብረተሰቡ በማንቃት ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ በመሆኑና ማህበራዊ ኃላፊነቱ በመወጣቱ ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል ያለው ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ በጎ ፍቃደኛ ወጣት ሐየሎም ዮውሀንስ ነው።

ወጣቱ እንደሚለው በአንድ ቀን የእጅ ንፅህና በመጠበቅ ብቻ ቫይረሱን ሙሉ በሙሉ መከላከል ባይቻልም ዋናው ህብረተሰቡን ነቅቶ በቀጣይነት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ለማስተማር እድል የሚሰጥ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም