የዓመታት ምኞትን በሰዓታት !

215

እንግዳው ከፍያለው ባህርዳር ዳር (ኢዜአ)

ከእንጦጦም ይሁን ከአዲሱ ገበያ፣ ከመገናኛም ይሁን ከቦሌ፣ ከጎተራም ይሁን ከሜክሲኮ..  ምን አለፋችሁ ከየትኛውም የአዲስ አበባ አቅጣጫ አሻግረው ሲመለከቱት ጥንታዊ ዛፎቹ ከቦታው ከፍታ ጋር ተዳምረው የወጣት ጎፈሬ መሰለው ይታያሉ ። ሁሉጊዜም አረንጓዴ ውበት የማይለየው ይህ ሥፍራ ለከተማዋ ታላቅ ድምቀት ሆኖ እስከ አሁን ድረስ ዘልቋል ።

ለወደፊትም ማራኪነቱ የበለጠ አምሮ፣ ተውቦ፣ ደምቆ፣ ፈክቶ… እንደሚቀጥል በሥፍራው እየተከናወኑ ያሉት ሥራዎችን አይቶ መተንበይ ነብይነትን አይጠይቅም።

አዲስ አበባ ለትምህርት በቆየሁባቸው ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አምስት ዓመታትም ሆነ ከዛ በኋላ ለሥራ በምሄድባቸው ጊዜያት የታላቁ የዳግማዊ ሚኒሊክ ቤተ መንግስትን በነፃነት ቀና ብዬ ለማየት የቻልኩበት እድል ገጥሞኝ አያውቅም። ቀደም ሲል በእንጨት ርብራብ አሁን ላይ ደረጃጃቸውን በጠበቀ መልኩ በኮንክሪት በተሠሩት ማማዎች ተንጠልጥለው የሚታዩት ቀይ መለዮ ያደረጉ ወታደሮችን ቀና ብሎ ለማየት ድባቡ ፍርሃትን ይለቁ ነበር ።

ለሥራ ወደ አዲስ አበባ በመጣሁባቸው ጊዜያት ከአራት ኪሎ ወደ ጊቢ ገብርኤልና ካዛንችስ ብዙ ጊዜ በእግሬ ተጉዣለሁ ። ቆም ብዬ በብረት አጥሩ ላይ (ቀኃሥ) ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ የሚለውን በአህጽሮተ ቃል የተጻፈውንና የሚኒሊክ ዘውድ፣ ጦርና ጋሻ ቅርጽ የያዘውን የብረት አጥር እንኳን ትኩር ብዬ ለማንበብ ስሞክር “አትንቀሳቀስም” የሚለው ቁጣ አዘል የወታደሮች ድምጽ ወደ ጆሮዬ ይመጣል።

ድምፃቸውን ስሰማ ፍርሀት አይሉት ጭንቀት የማላውቀው አንዳች ነገር ከራስ ጸጉሬ እሰከ እግር ጥፍሬ ያለውን መላ ሰውነቴን ሲወረኝ ይሰማኛል።

ተንቀሳቀስ ካለኝ ወታደር እይታ እስክሰወር ድረስ በደመ ነፍስና በመበርገግ ስሜት ፍጥነቴን በሁለትና ሶስት እጥፍ በመጨመር ተስፈንጥሬ ማለፌን የማውቀው ካሰብኩት ቦታ ከደረስኩ በኋላ ነው። ለነገሩ ብፈራና ብደንግጥ አይፈረድብኝም። ጊዜው ሲያልፍ የተፋጠጥኩት ገዢዎቻችን ከሚጠብቁ ልዩ የቤተ መንግስት ኮማንዶዎች ጋር መሆኑን ሳስብ እብደት መስሎ ይሰማኛል ።

 ምንም እንኳን ቀና ብዬ ላለማየት ወስኜ ለመራመድ ብሞክርም አላስችል እያለኝ ቀና ራመድ…ቀና ራመድ … እያልኩ የሄድኩባቸው ቀናት ብዙ ናቸው።

ከቀይ መለዮአቸው ጀምሮ የያዙት ዘመናዊ የጦር መሳሪያና ተክለ ቁመናቸው የሚያስፈሩት ኮማንዶዎች እንኳን እኔ አንድ ደካማ ምስኪን ቀርቶ ለሌላውንም ባለወኔ ነኝ የሚልን ጎረምሳ ያስፈራሉ። በአጥሩ የተጻፉትን እያነበብኩ ነው? እያየሁ ማለፍ አልችልም እንዴ?… የሚሉና ሌሎች ውሃ የማይቋጥሩ ክርክሮችን ማቅረብ በኮማንዶዎች ዘንድ ዋጋ የለውም። ሂድ ካሉህ መሄድ፤ ቁጭ በል ካሉህ እንደ እንጨት ደርቀህ ባለህበት ተኮርምተህ መቀመጥ ብቻ ነው የሚያዋጣው።

በአካባቢው በሄድኩባቸው ቀናት በህልሜም ሆነ በውኔ የሚመጣብኝ እንዲህ በሚጠበቀው ቤተ መንግስት ውስጥ ምን ይኖር ይሆን ? የሚለው ሃሳብ ነው። ለመሪዎቹ ሲባል ብቻ እንደዛ የተጠናከረ ጥበቃ የሚደረግ አይመስለኝም ነበር ። ምክንያቱም መሪዎቹን ለሥራ ወደ ምኖርበት አካባቢ ሲንቀሳቀሱ እኔም በሥራዬ ምክንያት ስለማገኛቸው ነው።

የቤተ መንግስቱን አጥር ትኩር ብሎ ማየት እንደ ትልቅ ወንጀል ታይቶ ተንቀሳቀስ ፣ ከዚህ ጥፋ የሚሉ ድምጾች በውስጡ ያለውን ሚስጢር የማወቅ ፍላጎቴ እንዲጨምር ቢያደርገውም "ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ" ሆኖብኝ ቆይቷል።

አሁን ላይ ጊዜ በጊዜ ተተክቶ ፣ ገዥዎችም ተቀያይረው… “ ታላቁ የአጼ ሚኒሊክ ቤተ መንግስት ” ለጉብኝት ክፍት ሆኖ ማየቴ ለእኔ ህልም ሆኖብኛል ። ለህዝብ ክፍት እንዲሆን ያደረገው ደግሞ የአንድነት ፓርክ በመገንባቱ ነው። የአንድነት ፓርክ እንዲገነባ ሃሳቡን ለጠነሰሱትና ላመነጩት ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድና ለሥራው መፋጠን ለተጉ ሙያተኞች የከበረ ምስጋና ባቀርብ የሚያንሳቸው እንጂ  አይበዛባቸውም ።

የአንድነት ፓርክ በመገንባቱ ለዘመናት በዙሪያው ባለው የአስፓልት መንገድ እየተጓዝኩ ሳልመው የነበረው የብዙ ጊዜ ፍላጎቴን ለማሳካት አስችሎኛል። በውስጥ ምን ቢኖር ነው?  እንደዚህ ከውጭ ለአይን እይታ እንኳን የሚከለከለው? የሚለውን የረጅም ዓመታት ጥያቄየም እነሆ ዛሬ ተፈትቷል ።

አጥሩን አልፌ ቤተ መንግስቱ ውስጥ ገብቼ ለመጎብኘት እድሉን ለማግኘት በቅቻለሁ። “እሹ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል” የሚለው የመጽሃፍ ቃል ሰምሮ እኔም የዘመናት ህልሜ ተሳክቷል።

እለቱ ቅዳሜ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም ነው። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች “በሚዲያ ስነ ምግባርና በለውጥ ሥራዎች ላይ ያካሄድነውን የሁለት ቀናት ስልጠና አጠናቅቀን በታላቁ የሚኒሊክ ቤተ መንግስት ውስጥ የተገነባውን የአንድነት ፓርክ እንደምንጎበኝ ሲነገረን ሁሉም ሠራተኛ ደስታው ወደር አልነበረውም። በተያዘው ፕሮግራም መሰረት በሁለት ፐብሊክ ሰርቪስ አውቶብሶች ወደ ቤተ መንግስቱ አመራን ።

በ1878 ዓ.ም እንደተገነባ የሚነገርለትና በ40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውን ታላቁን የሚኒልክ ቤተ መንግስት ለመጎብኘት የማይጓጓና የማይናፍቅ ያለ አይመስለኝም። በዓለም ላይ ሮማንያ የሚገኘው ፓርላሜንት ፓላስ 330 ሺህ ካሬ ሜትር ስኩየር ስፋት ያለው ታላቅ ፓላስ መሆኑን ዊክፒዲያ የተበላው የመረጃ ምንጭ ዘግቦት ይገኛል።

የኦስትሪያው ሆፍበርግ ፓላስ ደግሞ በ2ኛ ደረጃ ሆኖ ሲከተል የፈረንሳዩ ሎቨር ፓላስ በ3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በዚህ ደረጃ ቢካተት ኖሮ የአጼ ሚኒሊክ ቤተ መንግስት በስፋቱ 25ኛ ደረጃን መያዙ አይቀርም ነበር ብዬ አስባለሁ።

እኛም በአገራችን ታላቅ የሆነውን የአጼ ሚኒሊክ ቤተ መንግስት ለመጎብኘት ከአውቶቡስ ወርደን ከዋናው በር በስተግራ በኩል በተዘረጋው ድንኳን በር ተሰባስበናል ። ፍተሻውን ሁሉ አጠናቅቀን ወደ ዋናው በር ተጠጋን ።

ከበሩ አናት ላይ የሚኒልክ ዘውድ ካለበት ዋናው በር ፊት ለፊት ተራ በተራ እየተደረደርን ፎቶ በመነሳት አለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ ማለቱን ተያይዘነዋል ። በአዲስ አበባ ከካዛንችስ እስከ ብሄራዊ ቲያትር የተገነቡት ረጃጅም ፎቆች ብቅ ብቅ ብለው መታየት ከታላቁ ቤተ መንግስት ጋር በቁመት እኩል ለመሆን እየተፍጨረጨሩ ያሉ ይመስላል።

በሩን አልፈን እንደገባን “አንድነት ፓርክ የሚል ጽሁፍ ከስር ከአፍሪካ ምስል ላይ ፈርጠም ያለው የተጨበጠ እጅ የሚታይበት ሎጎ ፣ የትኬት መቁረጫ ቢሮ ፣ የገጸ በረከትና ማስታወሻ መደብሮችና ሌሎች ጽሁፎች በበራቸው ላይ የተጻፉባቸው ቢሮዎች አሉ።

እኛም በአንድ ላይ እንድንሰበሰብ ተደርጎ የፓርኩን ገጽታ የሚያሳይ ካርታ ታደለንና ምን ምን እንደምንጎበኝ ገለጻ ተደረገልን። በተለይም አትልክት ቦታዎችንና በነጭ የሴራሚክ ስብርባሪ የተሸፈኑ የመንገድ ዳር አካባቢዎችን መርገጥ እንደማይፈቀድ ገለጻ ያደረጉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የአንድነት ፓርክ ዋና ዳይሬክተር  ዶክተር ታምራት ሃይሉ ናቸው።

ወደ ውስጥ እንደዘለቅን “ኢትዮጵያ” በሚል ፊደል ተቀርጾ ከቆመው ጽሁፍ ሥር ፎቶ ማንሳትና መነሳት ተያይዘነዋል። በአጠገቡ የልብ ቅርጽ ያላት ፊደል ቀልቤን ገዝታዋለችል። የተቀባችው ቀለምም ደብዘዝ ያለ ሮዝ ወይም ቢጫ ቀለም ያለው ነው ። የልብ ቅርጿ ጥቁር ነጭ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ አፋር… ሳይል ሁሉም በአንድነት፣ በፍቅር… የመኖር ምስጢር አመላካች መሆኑን ሁሉም ጎብኚ በግቢ ውስጥ የሚያሳየውን ፍቅርና መረዳዳት በማየት መገንዘብ ችያለሁ።

ወደ ቀኝ በኩል ስናልፍ የተለያዩ በረግረጋማ መስክ የሚገኙ ነጫጭ የወፍ ዝርያዎች አረንጓዴ በለበሰው ሳር ላይ ተቀርጸው ይታያሉ። ወደ ላይ ቀና ሲሉ በነጭ፣ በሮዝ፣ በቀይና በሌሎች ቀለማት ያሸበረቀውን ዳገት ለተመለከተ ሰው “በተለያዩ ህብረ ቀለማት ያሸበረቀ ስጋጃ” የተነጠፈበት እንጂ መሬት ላይ በተተከሉ አበቦች መዋቡን መጠራጠሩ አይቀርም።

ለእኔ ደግሞ ከዛም አልፎ ሃዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” በሚለው መጽሃፋቸው ውስጥ የተጠቀሙትን ገለጻ እንዳስታውስ አድርጎኛል። ነገሩ እንዲህ ነው። እንዴት አትሉኝም? ሰብለወንጌል ከእልፍኟ በመውጣት በረንዳ ላይ ተቀምጣ የጧቷን ፀሃይ ስትሞቅ ሳሩ አብቦና በተለያዩ ቀለማት ፈክቶ ንቦች፣ ቢራቢሮዎችና ሌሎች ነፍሳት ሲራወጡበት ያየችውን ሜደ መስሎ በዐይነ ህሊናዬ ታየኝ ።

ለካስ የሁሉም ውበት ምንጭ መሬት ናት አልኩኝ በልቤ ። ከመስከረም ወር ጀምሮ በህብረ ቀለማት ወንዙ፣ ተራራውና ሜዳው ሁሉ አምሮና ተውቦ የሚደምቅባት ምድር ። የአንድነት ፓርክ ግን በሚደረግለት እንክብካቤ ዓመቱን ሙሉ ፈክቶ፣ አምሮና ተውቦ መታየቱ የተለየ ያደርገዋል።

ጉዞ  175 ሜትር ርዝመት ወዳለው የሰው ሰራሽ ዋሻ እያደረግን ነው ። ይህ ቦታ ጥቁር ጎፈር ያለው የአንበሳ መካን ነው ። ወንዱ አንበሳ በተሰራለት የእንጨት ርብራብ ቆጥ ላይ ራሱን ብቅ አድርጎ ይገማሸራል ። ሴቷ አንበሳ ደግሞ ፊቷን ወደ ወንዱ አንበሳ በማዞር ተጋድማለች ። ፍቅር የተፈጥሮ ስጦታ ነው ወይስ የልምምድ ውጤት የሚለውን ክርክር ያስታወስኩት በአንበሶቹ ነው ። ሴቷ አንበሳ የወንዱን አይን አይን ከታች ወደ ላይ አንጋጣ ታያለች ። ወንዱ አንበሳ ደግሞ የኛን ዱካ እያየ ከወዲያ ወዲህ እየተንቀሳቀሰ እሷ ላይ አደጋ እንዳይደርስ የሚጠብቅ ይመስላል።

በዋሻው ውስጥ ለውስጥ ስጓዝ በቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስትያናት የሚገኙትን ዋሻዎች በዐይነ ህሊናዬ እንዳስታውስ አድርጎኛል ። በዚህ ዘመን ይሄን ዋሻ በድንቅና ማራኪ ጥበብ መስራት መቻሉ አስደንቆኛል።

የውሃ ፏፏቴ ድምጽ በዋሻው ውስጥ ሲያልፉ ይሰማል። ዙሪያውን የትላልቅ ቋጥኝ ድንጋይ ተነባብረው እንደ አጥር በማገልገል ለአንበሳው ምቹ መኖሪያ ሆነዋል። በዋሻው ውስጥ ለውስጥ እያለፉም አልፎ አልፎ እንደ መስኮት ክፍት በሆኑት ቦታዎች አንበሳውን ማየት ይቻላል።

ዋሻውን አልፈው ወደ ላይ እንዳቀኑ የአረንጓዴ ስፍራ ይገኛል ። በዚህ የአረንጓዴ ቦታ ላይ ጤናዳም፣ በሶ ብላ፣ የስጋ መጥበሻ ፣ ፌጦ ፣ ነጭ ሽንኩርት… የሚባሉት አገር በቀል ተክሎች ይገኛሉ ። እንደ ማገጥ፣ የሰይጣን መርፌና ሌሎች የአረም ዝርያዎችም በዚህ ቦታ ይገኛሉ ።

ዋንዛና ዝግባ የመሳሰሉት ትላልቅ አገር በቀል ዛፎችም ይገኙበታል ። የአገር በቀል እፅዋቱ ለቅመማ ቅመም፣ ለመድሃኒትና ለውበት የሚያገለግሉ ናቸው ። የተለያየ ቀለም ያላቸው አበባዎች የሚያብቡ በመሆናቸው ደስታን ይፈጥራሉ ። አካባቢውን ግርማ ሞገስ አላብሰውታል።

ከዚህ ቦታ ላይ ሆኖ ካዛንችስን፣ 22ትን፣ ቦሌን፣ መስቀል አደባባይን፣ መገናኛንና ሌሎች በርካታ የአዲስ አበባ ሰፈሮች በቀላሉ ለማየት የሚያስችል ምቹ የመጎብኛ ቦታ ነው። ለነገሩ ቦታው ለአብያተ መንግስትነት መንበር የተመረጠውምኮ ገዥ ቦታ በመሆኑ ነው ።

ትንሽ ከፍ ብለው እንደተጓዙ ዘመናዊ ሎጅ የመሰሉ ክብ ቤቶች ተያይዘው ተገንብተዋል ። ቤቶቹ ከውጭ ሲታዩ በዶላር ወይም በፓውንድ የሚከራዩ መኝታ ቤቶች ነው የሚመስሉት ። አሠራራቸውም በላስታ ላሊበላና ሰቆጣ አካባቢ ከሚገኙ ህድሞ ቤቶች ጋር ቅርበት አላቸው ።

እነዚህ ከጣራቸው ላይ በእሬት ቁርጥራጭ ክዳን የተሰራላቸው ጎጆ የመሰሉ ቤቶች እጅግ ማራኪ ናቸው ። ቤቶቹ የኢትዮጵያውያውንን የቤት አሠራር አሻራ የሚያሳዩ ናቸው ።  ወደ ቤቶቹ ጠጋ ብየ ማረጋገጥ እንደቻልኩት ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች ናቸው። ውበታቸውን ያየ ሰው መጸዳጃ ቤት ይሆናሉ ብሎ የሚገምት አይኖርም። እኔም አልገመትኩም። ውስጣቸውም እጅግ ያማረና ማራኪ መሆኑን አንገቴን በማስገባት ማረጋገጥ ችያለሁ።

የእግረኛ መንገዱ የዳማ ወይም ቼዝ መጫወቻ ሰሌዳ የመሰለ በአረንጓዴ ሳርና በድንጋይ ንጣፍ የተሠራ መተላለፊያ አለ ። “አረንጓዴ ቦታውን ሳይረግጡ ይለፉ” የሚል ቢለጥፍም አሠራራቸው ጠመዝማዛ በመሆኑ በተነጠፈው ድንጋይ ብቻ ለማለፍ አስቸጋሪ ነው ።

የድንጋይ ንጣፉን ብቻ እየረገጡ ለማለፍ ሲሞክሩ ተንገዳግደው ሳሩን እየረገጡ ያለፉ ሰዎች መኖራቸውን አይቻለሁ። ለነገሩ እኔም ሁለት ጊዜ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሞኛል።

አገር በቀል ተክሎችን ወደ ቀኝ እየተዉ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ሲጓዙ የአረንጓዴ ሥፍራ ያገኛል ። አረንጓዴ ስፍራው ዘመናዊ ስታዲዮም ላይ የተነጠፈ ሰው ሰራሽ ሳር እንጂ ሌላ አይመስልም ። የሰላም ምልክት ተደርጋ የምትጠቀሰው ነጭ ርግብ እዚህ ቦታ ላይ በትልቁ ተቀርጻ ትገኛለች። ክንፎቿን ዘርግታ ስትታይ ሰላም አስፍኑ፣ ፍቅርን ፍጠሩ፣ ተሳስባችሁና ተመካክራች ኑሩ ... እያለች የምትሰብክ ትመላለች።

ፒኮክ እየተባለች የምትጠራው የወፍ ዝርያ ቅርጽ በአበባ ተቀርጻ የምትገኘው እዚህ ቦታ ላይ ነው ። በእውን ያለች እንጂ በምስል ተሰርታ የተቀመጠች መሆኑ ያጠራጥራል። ክንፎቿን ወደ ኋላ ዘር በማድረግ አንገቷን ቀና አድርጋ ትታያለች። ይህም ወፏን በአካል አይተን ለማናውቅ ምስሏን በማየት በቀላሉ ለመረዳት ያስችላል። በተለይም ለህጻናት በቀላሉ ለመገንዘብ ያስችላቸዋል።

የአረንጓዴ ስፍራውን ለማሳመርም 600 የጭነት መኪና አፈር ከሌላ ቦታ ተጓጉዞ ጥቅም ላይ መዋሉን ዶክተር ታምራት ሃይሉ አብራርተዋል ። እንደ ዶክተር ታምራት ገለጻ የአንድነት ፓርክ ለ130 ዓመታት ተዘግቶ የነበረውን ቤተ መንግስት አቧራውን በማራገፍ፣ በማደስና አዳዲስ ልማቶችን በፍጥነት በማከናወን ለህዝብ ክፍት ያደረግንበት የውጤታማነታችን ማሳያ ነው ይሉታል ።

እዚህ ቦታ ላይ ሆኖ ወደ ምዕራብ ሲያዩ ታላቁ የአጼ ሚኒሊክ የግብር አዳራሽ ይታያል ። የግብር አዳራሹ ከትልቅነቱ የተነሳ ጣራው ላይ ሶስት ታላላቅ አዳራሾች ተገጣጥመው የተሰሩ እንጂ የአንድ አዳራሽ ጣራ አይመስልም ። የሚገርም ስፋትና ርዝመት አለው ።

የበሮቹና የመስኮቶቹ ቅርጻ ቅርጽ የጥንት አባቶቻችን የጥበብ አሻራ ማረጋገጫ ናቸው ። ለጥበብ የነበራቸው ትኩረት ምን ያህል ከፍ ያለ እንደነበር የሚያሳይ ነው ። ቀለሙም ምን አልባት በእድሳቱ ደምቆ ቢታይም የጥንቱን ይዘት በመያዝ የተከናወነ በመሆኑ እጹብ ድንቅ የሚያስብል ነው። በነጭ፣ በቀይ፣ በሰማያዊ፣ ሮዝና ሌሎች ቀለማት ደምቆ የሚታይ ሳቢና ማራኪ ነው።

ዋናው የአዳራሹ መግቢያ በምዕራብ አቅጣጫ ነው ። ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ሲጓዙ የፏፏቴ ድምጽ ይሰማል። የፏፏቴው ድምጽ ታላቅ ወንዝ ውስጥ የመገኘት ያህል ጥሩ መንፈስ እንዲሰማ ያደርጋል ። ይህም የተፈጥሮን ጸጋ በዓይን አይቶ ለማድነቅ፣ በጆሮ ሰምቶ ለመደነቅ፣ ዳስሶ ለመርካት የሚያስችል ፏፏቴ ነው።

አካባቢውን የተፈጥሮ ውበት ከማላበስ ባሻገር ፏፏቴው ሃይል ስላለው በሚረጨው ውሃ ከፀሃይ የሚወረወረውን ሙቀት በማቀዝቀዝ የአገር ውስጡም ሆነ የውጩ ጎብኚ እንደልብ እንዲንቀሳቀስ አስችሎታል። የግብር አዳራሹ ወደ ውስጥ ሲገቡ የኳስ ሜዳ እንጂ ከ130 ዓመት በፊት የተገነባ አዳራሽ አይመስልም ።

ፊት ለፊት የአጼ ሚኒሊክ ምስል በህይወት ያሉ መስሎ ይታያል ። ጥቁር ባርኔጣቸው፣ ሰማያዊ፣ ጥቁርና ነጭ ቀለም ያለው ካባቻውን ደርበው በዙፋናቸው ተቀምጠው ይታያሉ ። ምስላቸውን ተጠግቶ ለማየትና ፎቶ ለመነሳት ከበሩ ጀምሮ ረጅም ሰልፍ መጠበቅ ይጠይቃል።

የንጉሱ ምስል ወደ አለበት ቦታ መጠጋት አይቻልም ። ምክንያቱም በወፍራም ገመድ መሰል ነገር የተከለለ በመሆኑ በቅርብ ርቀት ሆኖ ከማየት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም። ተራ በተራ ወደ ገመዱ እየተጠጉ ፎቶ መነሳቱን ሁሉም ጎብኚዎች ተያይዘውታል ።

ህጻናት ፣ አዛውንት፣ ወንድ ሴት፣ ፈረንጅ አባሻ… ብሎ ነገር የለም ሁሉም እየገባ ፎቶ ይነሳል። ከምስሉ በስተግራ የተለያዩ የብርሌ ዓይነቶች ይገኛሉ ። የሚኒሊክ ብርጭቆ እየተባለ የሚጠራው መጠጫም በተለያየ አይነት ተደርድረዋል።

አለፍ ሲሉም ከእንጨት የተሰራው የጠጅ መጥመቂያ ጋንና ሌሎች ከእንጨትና ከቆዳ የተሰሩ የጥንት ቅርሶች ይታያሉ ። በግብር አዳራሹ ሲያገለግሉ የነበሩ ቁሳቁሶችን ለማሰባሰብና ከነ ሙሉ ገጽታው ለጎብኚዎች ለማሳየት ጥረት እየተደረገ እንዳለ አማላከች ነው ።

ሁሉም መገልገያ እቃዎች በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት ለመኳንት፣ መሳፍንት፣ ቀሳውስትና ለሌላው ማህበረሰብ ግብዣ የሚቀርብበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። ዘመንን በአይነ ህሊና ወደ ኋላ ተጉዞ ለሚቃኝ ሰው በዛን ጊዜ የነበረውን የግብዣ ሁኔታ ምን እንደሚመስል መገንዘብ አያዳግትም።

ከግብር አዳራሹ ወደ ቀኝ በኩል ኢትዮጵያን በታላቁ ቤተ መንግሰት ሆነው አገርን የመሩና ያስተዳደሩ የሰባት ነገስታት ምስል የያዘ ግንብ ይገኛል ። ምስላቸው ከግራ ወደ ቀኝ አጼ ሚኒሊክ፣ ልጅ እያሱ፣ እቴጌ ዘውዲቱ፣ አጼ ሃይለ ስላሴ፣ መንግስቱ ሃይለ ማርያም፣ መለስ ዜናዊና አቶ ሃይለ ማርያም ደሳለኝ ናቸው።

 ወደ ቀኝ በኩል ትንሽ እንደተጓዙ በደርግና በኢህዴግ ዘመን የታንክ መጠገኛ ጋራዥ የነበረው ቦታ አሁን ላይ የሲኒማና የጭውውት ማሳያ መድረክ ተገንብቶበታል ። ከጎኑም የጥንቱ የቤተ መንግስት ዘመን ጠገብ ዛፎች ከስራቸው ተገርስሰው ወድቀው ይታያሉ ። በስራቸውና በግንዳቸው ላይ የእንስሳት፣ የወፎችና ሌሎች ቅርጻ ቅርጾች ተቀርጸው የፓርኩ አካል ሆነዋል ።

የአንድነት ፓርክ ለጎብኞች ክፍት የሆነው በያዝነው ዓመት ቢሆንም እስካሁን ከ200 ሺህ በላይ ህዝብ እንደጎበኘው ዶክተር ታምራት ገልጸውልናል ። የጎብኚዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝ ተመልክቷል።    የጉብኚቴ ሁለተኛው ክፍል በሌላ ጊዜ ይቀጥላል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም