በኢትዮጵያ የኮረናቫይረስን ለመከላከል ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቧል

62

በኢትዮጵያ የኮረናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከውጭ የተገኘ ድጋፍን ጭምሮ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ መመደቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከክልል ፕሬዚዳንቶችና የጸጥታ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ጋር የኮሮናቫይረስን መከላከ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ወቅት አንደገለጹትም ሃብት በማሰባሰብ ወረርሽኙን በተሟላ መንገድ ለመቆጣጠር ከክልል መንግስታት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል።

አጋጣሚውን ተጠቅመው ትርፍ ለማካበት ጥረት የሚያደርጉ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሰው ህይወት የማትረፍ ፍላጎት ያላቸው ነጋዴዎች ከመንግስት ጎን እንዶቆሙም ጠይቀዋል።

ወረርሽኙ የአለምን ምጣኔ ሃብት በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተነ በመሆኑ ቸል ሳይባል የሁላችንንም ትብብር ይጠይቃል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር አብይ።

በመሆኑም ያደጉት አገሮች የአፍሪካን ኢኮኖሚ ለመታደግ ቁርጠኛ አቋም እንዲወስዱ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

የአለም ባንክ ወረርሽኙን ለመከላከል ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አገሮች የመደበው ገንዘብ በቂ አለመሆኑን ገልጸው የG-20 አገራትና የተባበሩት መንግስታት ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ በፍጥነት ማድረስ ካልቻሉ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ሁኔታ ይደቃል ብለዋል።

''ያደጉት አገሮች አፍሪካ የበሽታ ጥቃት እዳይደርስባት መታደግና ኢኮኖሚው ሙሉ በሙሉ ወድቆ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የማድረግ ስራ የሚጠበቅባቸው በመሆኑ ሰፊ ስራ ተጀምሯል፤ ውጤቱም መጥፎ አይደለም'' ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም