በጎንደር ከተማ ተቋርጦ የቆየው የሆስፒታል ግንባታ ለማስቀጠል የቦታ ርክክብ ተካሄደ

86

ጎንደር ፣መጋቢት 14/2012 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ ላለፉት ሶስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የአይራ ጠቅላላ ሆስፒታል ግንባታ ለማስቀጠል የቦታ ርክክብ ተካሄደ።

የግንባታ ቦታው ርክክብ በተካሄደበት ወቅት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ክንዴሁን እገዘው እንደተናገሩት የሆስፒታሉ ግንባታ ሊቋረጥ የቻለው ከዚህ ቀደም በነበረው የስራ ተቋራጭ የአፈጻጸም ብቃት ማነስ ነው፡፡ 

ሆስፒታሉን በ2005 ዓ.ም  ግንባታው ተጀምሮ በ2009 ዓ.ም  ለማጠናቀቅ ቢታሰብም ከመጓተቱም በላይ ላለፉት ሶስት ዓመታት ስራው ተቋርጦ ቆይቷል።

ጤና ቢሮው አዲስ የግንባታ ጨረታ በማውጣትና አሸናፊ ተቋራጭ በመለየት በ280 ቀናቶች ቀሪ የግንባታ ስራዎቹን አጠናቆ እንዲያስረክብ ውል መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

ግንባታውን የጀመረው ተቋራጭ በህግ አግባብ የነበረበትን ቀሪ ገንዘብ በማስመለስ ከስራው እንዲወጣ ተደርጓል።

400 የህሙማን አልጋዎች የሚኖሩት ሆስፒታሉ እስካሁን 180 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ጠቁመው ለቀሪው ስራ ደግሞ የክልሉ መንግስት 85 ሚሊዮን ብር መመደቡን አመልክተዋል፡፡ 

የተመላላሽና የቀዶ ህክምና፤ የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት፣ የማህጸንና ጽንስ፣ የቤተ ሙከራና ሌሎችም ክፍሎች እንደሚኖሩት አቶ ክንዴሁን ገልጸዋል።

ግንባታውን በተቋራጭነት ያሸነፈው ድርጅት ኃላፊ አቶ አያሌው አዲሱ ቀሪ የግንባታ ስራዎችን በመለየት በገቡት ውል መሰረት አጠናቀው ለማስረከብ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉ ጎንደር ከተማን ጨምሮ ለማዕከላዊ ሰሜንና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ ግንባታው እንደተጀመረ ያመለከቱት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረሰኘ ፈንቴ ናቸው።

ይህም በጎንደር ዩንቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚስተዋላውን የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጫና በመቀነስ የህብረተሰቡን እንግልት ለማስቀረት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

መምሪያው የሆስፒታሉ የማጠናቀቂያ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ 

ሆስፒታሉ ከ300ሺ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና አገልግሎት የመስጠት አቅም እንደሚኖረው ግንባታው በተጀመረበት ወቅት መገለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም