በኒውዮርክ ከተማ የህክምና መሳሪያዎች ዕጥረት ሳቢያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ሊጨምር ይችላል

66

መጋቢት 14/2012 (ኢዜአ) በኒውዮርክ ከተማ በወሳኝ በሆኑ የህክምና መሳሪያዎች ዕጥረት ሳቢያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ሊጨምር እንደሚችል የከተማው ከንቲባ ማስታወቃቸውን ቢ ቢ ሲ ዘገበ።

የህክምና መሳሪያዎች ዕጥረት በተለይም ከአስር ቀናት በኋላ በስፋት እንደሚኖር የከተማው ከንቲባ ቢል ዲ ብላሲኦ ተናግረዋል።

“ተጨማሪ የአየር ማቀዝቀዣዎችን ማግኘት ካልቻልን የሰዎች ህይወት ያልፋል” ማለታቸውም ተገልጿል።

ሁሉም አሜሪካውያን ግልጽ የሆነውን ዕውነት ማወቅ እንደሚገባቸውም ሚስተር ዲ ብላሲኦ ለኤን ቢ ሲ መናገራቸውም ተጠቅሷል።

የቫይረሱ ስርጭት እየተባባሰ መምጣቱና ቀጣይ የሚያዚያና የግንቦት ወራት ስርጭቱ የከፋ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

በአሜሪካ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች 50 በመቶ የሚሆኑት በኒውዮርክ ስቴት እንደሚገኙ ተመልክቷል።

በአገር አቀፍ ደረጃ 31 ሺህ 57 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ፤ የ390 ሰዎች ህይወትም አልፏል።

በአንድ ቀን ውስጥ በኒውዮርክ ከተማ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ መረጋገጡ ነው የተገለጸው።

በትላንትናው ዕለት የኒውዮርክ ስቴት አስተዳደር አንድሪው ሱኦሞ በከተማው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 15 ሺህ 168 መድረሱን አስታውቀዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰቱት የኮሮና ቫይረስ ኬዞች 5 በመቶ የሚሆነው በኒውዮርክ መመዝገቡ በዘገባው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም