በክልሉና አካባቢው ኮሮናን የመከላከሉ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳደር ኦርዲን በድሪ አሳሰቡ

114

ሐረር፣  መጋቢት 13 / 2012 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል እና አካባቢው ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት የኮሮና ቫይረስን የመከላከሉን ስራ ማጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አሳሰቡ።

የሐረሪ ክልል፣የምስራቅ ሐረርጌ ዞን፣የሐረማያ ዩኒቨርሲቲና የምስራቅ ዕዝ አመራሮች በሽታውን ለመከላከል እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ዙሪያ ዛሬ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት በክልሉና አካባቢው በህብረተሰቡ ዘንድ አልፎ አልፎ መዘናጋትና ቸልተኝነት ይስተዋላል።

በተለይም በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የህብረተሰብ  ክፍሎች ያላቸው ማህበራዊ ትስስር ልማድ በመሰብሰብና  ቅርርብ የሚከናወን ነው፤ ይህም ለበሽታው ስለሚያጋልጥ  ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።

በክልሉ ቫይረሱን ለመከላከል ከውሃ አቅርቦትና  ገበያ ማረጋጋት ጋር በተያያዘ  እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ወደ ክልሉ የሚመጡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ጥንቃቄው እንዳለ ሆኖ ኢትዮዽያዊ በሆነ መልካም ስነ ምግባር ማስተናገድና አገልግሎት መስጠት እንደሚያስፈልግም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የውሃ እጥረት እንዳያጋጥም እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት የክልሉ  ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ናቸው።

ለዚህም 1ሺ ሊትር የሚይዝ የውሃ ታንከር በስምንት የተለያዩ ቦታዎች በማስቀመጥ ህብረተሰቡ እንዲጠቀም ተመቻችቷል።

በቀጣይም በከተማውና ገጠር  አስር  ቦታዎች ላይ ተመሳሳይ የአቅርቦት ስራዎች ይከናወናል ብለዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሶ በበኩላቸው በዞኑ የኮረና ቫይረስን ለመከላከል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም በሽታውን ለመከላከል በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት  ከመፈጸም አንጻር በአመራሩ በኩል ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል።

በጅምር ያሉ ስራዎችን ማጠናከርና ወደታችኛው የህብረተሰብ ክፍል በመዝለቅ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚሁ ዞን  ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመዲን ከቢር ሁሴን እንዳሉት በምስራቅ ሐረርጌ  5ሺ ለሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች  ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን ገልጸዋል።

በየወረዳዎች ፣  ቀበሌ ገበሬ ማህበርና ከተሞች ውስጥም  የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

በዞኑ 127 በሚሆኑ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ውስጥ ለይቶ ማቆያ ክፍሎች መዘጋጀታቸውንም አመልክተዋል።

በከተማው በሚገኙ ጭፈራ ቤቶች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የሐረሪ ክልል ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ናስር ዮያ ተናግረዋል።

23 የሺሻ መጠቀሚያ እቃዎች በቁጥጥር ስር ውለው መወገዳቸውንም ጠቁመዋል።

በውይይቱ የመረጃ ልውውጥ፣ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ቅንጅታዊ አሰራርና ግብዓትን ማሟላት በሚቻልበት  ዙሪያ ተሳታፊዎች መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም