የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ስለ ኮሮና ቫይረስ የተለያዩ መረጃዎችን የሚሰጥ ሲስተም ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

142

አዲስ አበባ፣መጋቢት 13/2012 (ኢዜአ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝና የተለያዩ መረጃዎችን የሚሰጥ ሲስተም ተግባራዊ ሊያደርግ ነው።

ኤጀንሲው የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ሥርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ “የኢትዮጵያ የተቀናጀ የኮቪድ-19 መቆጣጠሪያ ሲስተም" ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

በነገው ዕለትም የጤና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በይፋ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር መሆኑን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኤጀንሲው ያዘጋጀው ሲስተም ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ወቅታዊ የኮሮና መረጃዎችን ማድረስ እንዲሁም ገለጭ የቦታ ማሳያዎችን ለማየት የሚያገለግል ይሆናል።

ስለ ኮሮና ቫይረስ ምልክቶች፣ ጥንቃቄዎች፣ ህክምና እና ሌሎች መረጃዎችን ለማግኘት፤ ዜጎች በራሳቸውም ሆነ በሌሎች ላይ የሚያጋጥሟቸውን ጥርጣሬዎች ሪፖርት ለማድረግም የሚጠቅም መሆኑ ተገልጿል።

ሲስተሙ የተለያዩ ሙያ እና አቅም ያላቸውን በጎ ፈቃደኞች ለመመዝገብ፤ እርዳታዎችን በአይነትም ሆነ በገንዘብ ለመሰብሰብ እንዲሁም ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ የመረጃ  ምንጮችን (ሊንኮችን) ለመጠቆም ያግዛል ተብሏል።

እንደ ሆስፒታል፣ ፋርማሲ፣ ፖሊስ ጣቢያ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለማመላከትና መረጃዎችን ለማሰራጨትም የሚያገለግል መሆኑ ተመልክቷል።

የመከላከያና መቆጣሪያ ሲስተሙ ቫይረሱ ሊያስከትል የሚችለውን የከፋ ሁኔታ ከወዲሁ ለመከላከልና ጥንቃቄ ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ኤጀንሲው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም