ሰላምን በሚያውኩ እንቅስቃሴዎች ላይ ክትትል እንዲደረግ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ

89

ጎንደር ፣ መጋቢት 13/2012 (ኢዜአ) የጎንደር ከተማ ጸጥታን በሚያውኩ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ ተገቢው ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ የከተማው ነዋሪዎች ጠየቁ።

ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ነዋሪዎች በከተማው ጸጥታ ጉዳይ በጎንደር ከተማ እየመከሩ ነው

የምክክሩ ተሳታፊ አቶ አንተነህ ሲሳይ እንዳሉት በከተማዋ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ ክፍተት በመኖሩ ህገ-ወጥነት እየተበራከተ መምጣቱ አሳስቧቸዋል።

በተለይም በተለያዩ ቡድኖች እየተሰባሰቡ የሚንቀሳቀሱ አካላት ለከተማው ሰላምና ደህንነት ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውንም ጠቅሰዋል።

ህዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም ለመግባት ተቸግሯል፣ ዝርፊያና ህገ-ወጥነት የከተማዋ መገለጫ እየሆነ የንግድ እንቅስቃሴውም እየተዳከመ እንደመጣ አመልክተዋል።

ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘም በማህበራዊ ድረ-ገጾች የከተማዋን ደረጃ የማይመጥን ወሬ ላይ መንግስት በወቅቱ መረጃ አለመሰጠቱም ችግር መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ንጉስ አሰፋ ናቸው።

በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ ህገ-ወጥነትን በማረም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና የተረጋጋ ሰላም ለመፍጠር ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በምክክሩ ላይ የተገኙት የከተማው ተቀደሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም በበኩላቸው ከተማዋ ለኑሮም ሆነ ለንግድ እንቅስቃሴ የተመቸች እንድትሆን ሰላምን ለማስከበር ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

"የከተማ አስተዳደሩ የፀጥታ መዋቅሩን በማደራጀት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እቅድ ይዞ እየሰራ ቢሆንም የሚጠበቀውን ያህል ውጤታማ መሆን አልተቻለም"ብለዋል።

በተለይም አልፎ አልፎ የሚነሱ አለመረጋጋቶች የከተማዋን የቀደመ ስም የሚያጎድፉ እየሆኑ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።

የተረጋጋ ሰላምን ለማረጋገጥ የከተማ አስተዳደሩ የሚያደርገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ህገ-ወጦችን በማጋለጥ ረገድ የነዋሪዎቹ አስተዋጽኦ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም