ታታሪነቱን የገታው…

79

ብርሃኑ አለማየሁ ( ኢዜአ)

ወጣት አእምሮ አወቀ ይባላል። በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ መነን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ  በአነስተኛ ሱቅ የተለያዩ ሸቀጦችን በመሸጥ የእራሱንና የቤተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ደፋ ቀና ይላል፡፡ አእምሮ የወጣትነት ጉልበቱን በመጠቀም የነገ ስኬቱን አልሞ በማለዳ በመነሳት እስከ ምሽት ከትንሿ ሱቅ አይለይም፡፡

ታዲያ ከዕለታት በአንዱ ቀን እንደተለመደው የእለት ስራውን አከናውኖ ከጨረሰ በኋላ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ ሱቁን ዘግቶ እንደወጣ ወጣቱን ያላሰበው አደጋ ይገጥመዋል። ከስራ ድካም ለማረፍ ወደ ቤት እያቀኑ የነበሩት የወጣቱ እግሮች ከመንገዳቸው ታግተው በሰፈሩ ሲዘዋወር በነበረ ውሻ ይነከሳሉ፡፡
ወጣት አእምሮን ጨምሮ ሌሎች ሶስት ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰው የሰፈሩ ውሻ ባለቤት አልባ እንደሆነ ነው የኋላ ኋላ የታወቀው። በውሻው ከተነከሱት መካከል ወጣት አእምሮም በወቅቱ በደረሰበት ንክሻ ከስራ የማይቦዝኑት እጆቹ ያለስራ እቤት ውለው እቤት ካደሩ ቆይተዋል፡፡

ወጣቱ በውሻው ከደረሰበት ንክሻ በኋላ የክትባት ህክምናውን ሲከታተል ቢቆይም በአስራ አራተኛው ቀን ያጋጠመው ግን በበሽታው ምክንያት ራስን ከመሳት አልፎ የሰውነቱ አለመታዘዝ  የአልጋ ቁራኛ እንዲሆን አስገድዶታል፡፡ ታታሪነቱም እዛው እንዲገታ አደረገው።

በአሁኑ ወቅትም ባለቤት አልባ ውሾች የከተማዋን ነዋሪዎች ስጋት ከመሆን አልፎ በማህበራዊ ህይወታቸውና በጤናቸው ላይ ትልቅ ችግር አየሆነ መምጣቱ ነው የሚስተዋለው። የባለቤት አልባ ውሾች መስፋፋትና እሱን ተከትሎ የሚመጣው የእብድ ውሻ በሽታ ከስጋትነት ተሻግሮ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል፡፡ በየአካባቢው ያለው የአስተዳደር አካላት ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጡ ነዋሪዎቹ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም መፍትሔ ግን እየተሰጠው አለመሆኑን ነው የሚነገረው።

የእብድ ውሻ በሽታ በቫይረስ  አማካኝነት  በበሽታው  ከተለከፈ እንስሳ ወደ ሌላ ጤነኛ እንስሳ ወይም ወደ ሰው በንክሻ የሚተላለፍ ሲሆን ሰውን ጨምሮ ሁሉንም  ደመ  ሞቃትና አጥቢ  እንስሳን  የሚያጠቃ  ነው፡፡  በሽታው  በአብዛኛው  በውሾች  ላይ  ስለሚታይና ሰዎችም  የሚገነዘቡት ይሄንኑ በመሆኑ የእብድ ውሻ በሽታ የሚል ስያሜ እንደተሰጠው መረጃዎች ያሳያሉ።  

በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተላለፉ በሽታዎች ላይ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ባዬ አሸናፊ እንደነገሩን ከሆነ በሽታው በቫይረስ የሚመጣ ሲሆን በአእዋፋትና በሌሎች ተሸካሚ አካላት አማካኝት ከቦታ ቦታ የሚሰራጭ ነው፡፡ መፍዘዝ፣ መቅበዝበዝ፣ማላዘን እንዲሁም ውሃ፣ ምግብ፣ ድምጽና ፉጨት መፍራት በውሾች ላይ በበሽታው ወቅት የሚታይባቸው ምልክቶች እንደሆኑ ተመራማሪው ይጠቅሳሉ።

በሽታው ወደ ሰዎች ከተተላለፈ በኋላ ዋና መሰራጫውን ጭንቅላት ላይ አድርጎ ሁሉንም የሰውንት እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ትኩሳት፣ ሲቆይ ደግሞ ማስታወክ፣ ማስቀመጥ፣ የሆድ ህመም፣ ድምጽና ብርሃንን የመፍራት ሁኔታዎችን እንደሚያሳይም ነው ባለሙያው የሚናገሩት። ህመሙ እየከፋ ሲሄድ መቆጣጠር እንደማይቻልና ለሞት እንደሚዳርግም ይገልጻሉ።

እንደ ዶክተር ባዬ ገለጻ የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ለጥናት ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ባቀኑበት ወቅት በሽታው በመላ አገሪቱ  በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ማየታቸውንና ህብረተሰቡም የእብድ ውሻ በሽታን እንደ መልካም አስተዳደር ችግር በመቁጠር ጥያቄ እያቀረበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የበሽታውን የጉዳት መጠንና የስርጭት ስፋት ለማወቅ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰሩ ያሉ ጥናቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን በመጠቆም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ7ሺ በላይ ሰዎች ከእብድ ውሻ በሽታ ጋር በተያያዘ ህክምና ማድረጋቸውንና 20 ዎቹ ደግሞ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ነው ዶክተር ባዬ የነገሩን።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽን በበኩሉ በሽታው የሚታይባቸው ውሾችን የመግደል ስራ ማስቀረቱንና በስጋ የሚሰጠው መግደያ መድሃኒትም ወደ አገር ውስጥ መግባት  ማቆሙን በማውሳት፤ በአለም አቀፍ ደረጃ የአለም ጤና ድርጅትም የመድሃኒቱን ስርጭት ማገዱን ነው የተገለጸው።

በኮሚሽኑ የእንስሳት ጤና ዳይሬክተር ዶ/ር ፋሲካ በለጠ እንደሚሉት እስከ ያለፈው የካቲት ወር ድረስ ከ12 ሺ በላይ ውሾች መከተባቸውንና የጎዳና ውሾቹን ለተከታታይ አምስት አመታት በመከተብ በሽታውን የመከላከልና የማጥፋት እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በየክፍለ ከተማው የጎዳና ለይ ውሾች በሚበዙበት ቦታዎችን በመለየት ክትባቱን የመስጠት ስራዎች መከናወናቸውንም ነው ያስረዱት፡፡

ክትባቱን ከወሰዱት ውጪ ከዚህ ቀደም በሽታው የታየባቸውን ውሾች ለማስወገድ ከደቡብ አፍሪካ መድኃኒቱን በማስገባት ላይ እንደሚገኙ  የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጋር በጋራ በመሆን በተሰራ ስራ ሁለት  መድኃኒቶች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በከተማ ደረጃ በዚህ በጀት አመት ከእንስሳት ወደ ሰው በሚተለላፉ በሽታዎች ላይ በዋናነት ደግሞ የእብድ ውሻን በተመለከተ ጥናት በመደረግ ላይ መሆኑን የነገሩን ዶ/ር ፋሲካ፤ በያዝነው ወር መጨረሻ ጥናቱን ይፋ በማድረግ   በሽታውን  የበለጠ ለመቆጣጠር ምን መደረግ እንዳለበት አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ  በእብድ  ውሻ በሽታ  ምክንያት  በየአመቱ ከ60ሺ በላይ የሰዎች ሞት የሚመዘገብ ሲሆን ከ90 በመቶው በላይ የሚሆነው ሞት የሚከሰተው በእስያ እና አፍሪካ ውሥጥ ባሉ አገራት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ህብረተሰቡ በቤቱ ውስጥ የሚያሳድጋቸውንም ሆነ በየአካባቢው የሚገኙትን ውሾች  የጤና ባለሙያዎች በየጊዜው ለክትባት ሲሄዱ ማስከተብ እንዳለባቸውና ውሾቹ ላይ የተለየ የጤና መታወከ ሁኔታ ሲታይ ደግሞ በአቅራቢያ ላሉ የጤና ተቋማት መጠቆም እንደሚገባም ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።

ሰዎች በውሻም ይሁን በሌሎች ደመ ሞቃታማ እንስሳት የመነከስ አደጋ ካጋጠማቸው በኋላ ቶሎ ወደ ህክምና የሚሄዱ ከሆነ በበሽታው የመያዝና የመሞት እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑንም የሚናገሩት ባለሙያዎቹ፤ አንድ ሰው በአበደና አብዷል ተብሎ በተጠረጠረ እንስሳ ቢነከስ  ንክሻው  ወደ  ሌላኛው የሰውነት ክፍል  እንዳይዛመት ቁስሉን  ሳይጫን   በውሃና   በሳሙና   በማጠብ   የመጀመሪያ   የሕክምና  ዕርዳት ሊያገኝ  ወደሚችልበትና ከበሽታው  ጋር  በተያያዘም  የምክር  አገልግሎት ወደ ሚሰጥበት ጤና  ተቋም መሄድ እንዳለበት ይመከራል።

ንክሻው ከባድና በተለይም ከአንገት በላይ የተፈጸመ  ከሆነ እንዲሁም  ሰፋ ያለ ቦታ  የሚሸፍን  ጉዳት የደረሰበት ግለሰብ የመከላከያ ክትባት ወዲያውኑ መጀመር ግዴታ መሆኑንም ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም