በማረሚያ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት የኮሮናን በሽታ የመከላከል ተግባር እየተከናወነ ነው

60

አሶሳ ፣ መጋቢት 12 / 2012 (ኢዜአ)  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማረሚያ ቤቶች ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የኮሮናን በሽታ የመከላከል ተግባር እያከናወነ መሆኑ ተገለጸ፡፡ 
የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር አቶ ዘላለም ጃለታ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ አሶሳ ፣ ካማሽ እና መተከል ዞን ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎች ከበሽታው ለመከላከል እየተሰራ ነው፡፡ 

የህግ ታራሚዎቹን ከኮሮና ቫይረስ አስቀድሞ ለመከላከል ከትናንት ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው እንዳይገናኙ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

"ከቤተሰቦቻው የሚመጡ ምግብ ፣ አልባሳት እና ሌሎችም መልዕክቶች ግን ለጊዜው ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው " ብለዋል፡፡

የማረሚያ ቤት ፖሊሶች፣ ሲቪል ሠራኞች እንዲሁም ወደ ህክምና እና ሌሎች ጉዳዮች የሚወጡት እና የሚመለሱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በወንጀል ተጠርጥረው ለሚመጡ አዲስ ግለሰቦች ደግሞ የተለየ ማረፊያ ተዘጋጅቷል፡፡

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተወካይ አቶ ከበደ ጉዳያ በበኩላቸው በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከል እስከ መጋቢት 24/2012 ዓ.ም የሚካሄድ ችሎት እንደማይኖር ተናግረዋል፡፡

ሆኖም የህዝብን እና የሃገርን ጥቅም የሚጎዱ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከቱ ችሎቶች እንደ አስፈላጊነቱ በዝግ ሊታዩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ 12 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን ከበሽታው ለመጠበቅ ኮሚቴ አቋቁሞ ስራ መጀመሩን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ተፈሪ ሞላ ናቸው፡፡ 

ተማሪዎች ከአላስፈላጊ ንኪኪ ተጠብቀው በማደሪያቸው እርስ በእርስ እንዲማማሩ እየተደረገ መሆኑን አመልክተው፤ 

" ሳሙና፣ አልኮል እና ሌሎችን የንጽህና መጠበቂያዎች እየቀረቡላቸው ነው " ብለዋል፡፡

በአሶሳ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት፣ ሆቴሎች እና ሌሎች የሚገቡም ሆነ የሚወጡ ሠራተኞች እንዲሁም ባለጉዳዮች እጃቸውን በሳሙና እንዲታጠቡ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉ የኢዜአ ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቧል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እስካሁን የኮሮና በሽታ እንዳልተከሰተ ከክልሉ ጤና ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም