ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ የያዘችውን ምክንያታዊ አቋም አጠናክራ መቀጠል አለባት ... ምሁራን

74

ደሴ፣ መጋቢት 12/2012 (ኢዜአ ) ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ በተፈጥሯዊ ሃብቷ የማዘዝ መብቷን ለማረጋገጥ የያዘችውን ምክንያታዊ አቋም ሳይሸራረፍ ማስቀጠል ይገባታል ሲሉ የወሎ ዩንቨርሲቲ ምሁራን ገለፁ።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽመልስ ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓለም ካለው የውሃ ሀብት 3 በመቶ ብቻ ንጹህ በመሆኑ የውሃ ፖለቲካው ለጋራ ተጠቃሚነት መዋል  አለበት፡፡

ኢትዮጵያም የዓባይን ወንዝ የመጠቀም መብቷን የሚከለክላት ህግም ሆነ ፖለቲካዊ ምክንያት ሊኖር እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

ግብፅ በተለያዩ የአፍሪካና የዓለም አገራት የሀሰት መረጃዎችን በማቅረብ የህዳሴ ግድብ ግንባታውን ለማስቆም የምታደርገውን ከንቱ ድካም በመረጃ አስደግፎ በመከራከር ማክሸፍ አስፈላጊ እንደሆነ ምሁራኑ ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ከ86 በመቶ በላይ የውኃ ሀብት የሚመነጭባት አገር  ባለቤት ብትሆንም ብቻዬን ልጠቀም ባለማለቷ ልትመሰገን ሲገባት የበይ ተመልካች እንድትሆን መፈለጉ በየትኛውም አግባብ ተቀባይነት የለውም ብለዋል ፡፡

የአባይ ጉዳይ የኢትዮጵያን ህዝቦች ከድቅድቅ ጨለማ ከማውጣት ባለፈ ስር ከሰደደ ድህነት የመውጫ መንገድ በመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ቸል ሊባል አይገባም ሲሉ ምሁሩ ገልፀዋል።

የቀደሙ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የጎዱ ነበሩ ያሉት ምሁሩ አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያ ባለ ሙሉ መብት መሆኗን ለማስከበር እያደረገችው ያለው ጥረት በህግም ተቀባይነት ያለው ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን መስራት አለብኝ የራሴ ሀብት ነው፤ ጎረቤቶቼንም አልጎዳም፤ በጋራ እንጠቀም የሚለውን ምክንያታዊ አቋሟን ማስቀጠልና ለዓለም ማህበረሰብ ማስረዳት ይጠበቅባታል ሲሉም አብራርተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት መምህር አቶ አማረ አያሌው በበኩላቸው ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ በጦርነት ሳይሆን የምትታለለው በስምምነት አንቀፆች ላይ መሆኑን ጠቅሰው የውጫሌውን እንደማሳያ አንሰተዋል፡፡

በመሆኑም የማንም ጥገኛ ሳትሆን ድርድር በምታደርግበት ወቅት በጥንቃቄ ከምሁራንና ከህዝብ ጋር መምከር እንደሚገባ መክረዋል።

"በሀብቱ አጠቃቀም ዙሪያም በቀጠናው ያሉ አገሮች ብቻ ናቸው መወሰን ያለባቸው እንጂ ሌሎችን አይመለከታቸውም" ያሉት አቶ አማረ ከጋራ ጥቅም ውጭ አዛዥም ሆነ ታዛዥ መኖር የለበትም ብለዋል፡፡

ግብጽ በተለያዩ የዓለም አገራት የምታናፍሰው ውዥንብር፣ ፍርሃት፣ ወከባና ግድቡን ለማጓተት የሚደረጉ ሙከራዎች ለኢትዮጵያ የበለጠ ብርታት እንጂ ስጋት እንደማይፈጥር ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ አማራ ገለጻ ከሌሎች የአፍሪካና የዓለም አገሮች ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠርም እውነቱን ማስረዳት ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል፡፡

"ከ260 በላይ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ባለበት ዓለም ውስጥ ዓባይ ለብቻው ህግ አይወጣለትም" ያሉት በዩኒቨርሲቲው የስነ-ህይወት መምህር ዶክተር ሁሴን አዳል፤ ጫና በመፍጠር እንድትስማማ የተደረገውን ጥረት ኢትዮጵያ አልቀበልም ማለቷ ህዝብን ያኮራና የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

"ሁሉም አገራት ወንዛቸውን ገድበው የተፈጥሮ ሀብታቸውን በሚጠቀሙበት ዓለም የኢትዮጵያ በምን ይለያል?" ብለው የሚጠይቁት ዶክተር ሁሴን፤ ሱዳን አራት ግድቦችን ገንብታ እየተጠቀመች መሆኑን እንደ ማሳያ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምሁራንና ብዙሃን መገናኛ ተቋማትም ትክክለኛውን ሀሳብ በተለያዩ ቋንቋዎች ለዓለም የማሳየት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ በማሳሰብ፤ ህብረተሰቡም ከመንግስት ጎን በመቆም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ አጋርነቱን በባለቤትነት መንፈስ  በማሳየት መረባረብ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም