የሚኒስትሮች ምክርቤት ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት ሰባትን በሽብርተኝነት የፈረጀው አዋጅ እንዲነሳ ወሰነ

133
አዲስ አበባ ሰኔ 23/2010 የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባርን (ኦነግ)፣ የኦጋዴ ብሄራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) እና ግንቦት ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶችን በሽብርተኝነት የፈረጀው አዋጅ እንዲነሳ ተወሰነ። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው ድርጅቶቹ ከሽብርተኝነት ዝርዝር እንዲሰረዙ የወሰነው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት ሰባት የፖለቲካ ድርጅቶችን በሽብርተኝነት የሚፈርጅ አዋጅ ማውጣቱ የሚታወስ ነው። በዚህም በአሁኑ ወቅት ድርጅቶቹን በሽብርተኝነት የፈረጀውን አዋጅ እንዲነሳ ምክር ቤቱ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል። የአዋጅ ማሻሻያው ፓርቲዎች በአገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት 7 ከሽብርተኝነት ዝርዝር እንዲሰረዙ የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ እንዲፀድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩንም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም