በምስራቅ ወለጋ ዞንና በነቀምቴ ከተማ የተረጋጋ ሁኔታ ተፈጥሯል

57

ነቀምቴ ፣ መጋቢት 12/2012( ኢዜአ) በምስራቅ ወለጋ ዞንና በነቀምቴ ከተማ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በፈጠረው ቅንጅታዊ አሰራር የተረጋጋ ሠላም እየሰፈነ መምጣቱን ነዋሪዎች ገለፁ ።

የነቀምቴ ከተማ 05 ቀበሌ ነዋሪና የአገር ሽማግሌ አቶ ሽፈራው ፈለቀ በሰጡት አስተያየት የከተማው ሕዝብ የራሱንና የአከባቢውን ሠላም ለማረጋገጥ በየመኖሪያ አካባቢው  በመደራጀት የተረጋጋ ሰላም ለማስፈን ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን  ገልፀዋል ።

በዲጋ ወረዳ የጅራታ ቀበሌ ነዋሪ አባ ገዳ አስፋው ከበደ በበኩላቸው ሕዝቡ የአካባቢውን ሠላም ለማረጋገጥ አባ ገዳዎች ፣ የአገር ሽማግሌዎችና  የሃይማኖት አባቶች  ከሕዝቡ  ጋር  በየጊዜው በመወያየት ሰላም እንዲረጋገጥ ያከናወኑት ስራ ተጨባጭ ለውጥ እያሳየ  ነው ብለዋል ።

አጥፊዎች ሲገኙ በመምከር እንዲመለሱ በማድረግና የማይመለሱትን ደግሞ የሕግ  የበላይነትን ለማስከበር ለፀጥታ አካላቱ ጥቆማ በመስጠት የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ  እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል ።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ማዕከላዊ ሲኖዶስ የነቀምቴ  መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር ቄስ አሰፋው ተርፋሳ እንዳሉት ደግሞ ሠላም እንዲሰፍን ተከታታይነት ያለው ሃይማኖታዊ ትምህርት እየሰጡ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በከተማውና  በየወረዳዎቹ የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል ፡፡

የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ረቢቱ ደቻሣ በበኩላቸው በከተማው  ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ሕዝቡን በየፀጥታ ቡድን በማደራጀት በተሰራው ሥራ ለውጥ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

ሕዝቡ ሠላም ፈላጊ በመሆኑ ከፀጥታ አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር  ለፀጥታ  አስጊ  ናቸው ያላቸውን ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል  ብለዋል ።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን የአስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሻምበል  ኤቢዮ በበኩላቸው  በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎች የፀጥታ ችግር አለመኖሩንና ሕዝቡ  በሰላማዊ መንገድ መደበኛ ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም