የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት መከላከል በሚያስችል መልኩ ቀጥሏል

58

መቀሌ ኢዜአ መጋቢት 11/12 ዓም በትግራይ ክልል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት ለመከላከል በሚያስችል መልኩ እየተካሔደ መሆኑን የልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደሮች ገለፁ። 
በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በሓውዜን ወረዳ  ሰላም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ግርማይ ካህሳይ እንደተናገሩት በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ላይ  የኮሮና ቫይረስን አስከፊነት፣የበሽታው መንስኤና መከላከያ መንገዶቹ በቂ ግንዛቤ ተሰጥቶን እንድንሰራ ተደርጓል ብለዋል ።

በአካባቢያቸው የተጀመረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንዳይቋረጥ ተጋላጭነትን መከላከል በሚያስችል መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል ።

የራሳቸውና የአካባቢያቸው ንፅህና በመጠበቅና መጠጋጋትና ንክኪን በማስቀረት ቫይረሱን አስቀድሞ ለመከላከል ዝግጅት መደረጉን አርሶ አደር ግርማይ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል አርሶ አደሮች በአንድ ተሰባስበው ይሰሩት የነበረውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ባለሙያዎች  በሚሰጥዋቸው መመሪያ መሰረት በብዛት ሳይሰባሰቡ እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በደቡባዊ ምስራቅ ትግራይ  ዞን ደጉዓ ተምቤን ወረዳ ዓዲአዝመራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገብረ አብእዝጊ ገብረዮሃንስ ናቸው ።

በአካባቢያቸው ከሩቅ ቦታ በእንግዳነት የሚመጣ ሰው ከየት እንደመጣ  በመጠየቅ  ወደ ማህበረሰቡ ከመቀላቀሉ በፊት ከጤና ባለሙያዎች ጋር እንዲገናኝ  እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

የቫይረሱ ምልክት ትኩሳት፣ሳል፣የትንፋሽ መቆራረጥ እና የመተንፈስ ችግር እንደሆነ ከጤና ባለሙያዎችና  ከሚዲያ መከታተል ችያለሁ ያሉት ሌላው የትግራይ ምስራቀዊ ዞን አፅቢወንበርታ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሃይለ ስላሴ ተስፋይ ናቸው ።

የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ክፍሎም አባዲ በበኩላቸው አንድ ቤተሰብ አራት ሜትር ርቀት ጠብቆ  እንዲሰራ በማድረግ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራውን ሳይቋረጥ መቀጠሉን ገልጸዋል።

"ከስራ ሰዓት በኋላ በአንድ ላይ ሲደረግ የነበረ የውሎ ግምገማ እንዲቋረጥ ተደርጓል" ያሉት አቶ ክፍሎም የርቀት ቦታቸው ጠብቀው በቡድን 12 ሰዎችን  ብቻ ሆኖው  የውሎ ግምገማው  እንዲካሄድ እተደረገ ነው ብለዋል።

 በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ሳይታይ በአጭር ጊዜ  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው እንዲጠቃለል የቤተሰብ ሙሉ ጉልበት በመጠቀም እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

አርሶ አደሮች የኮሮና ቫይረስ  በሽታ በመፍራት ከስራ እንዳይስተጓጎሉ በጤና ባሙያዎች ክትትል እየተደረገ ይገኛል ያሉት ደግሞ የፅቢወንበርታ ወረዳ ጤና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረህፃን ገብረመስቀል ናቸው።

በሽታው በአርሶአደሮች እንዳይከሰት የወረዳው ጤና ባለሙያዎች ወደ ቀበሌዎች በመውረድ የኮሮና ቫይረስ ቫይረስ ምልክት፣መተላለፊያና መከላከያ መንገዶቹ የተመለከተ አስተምህሮ በስፋት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም