የአዲስ አበባ ጤና ጣቢያዎች የኮሮና ቫይረስ መዛመትን ለመከላከል እየሰሩ ነው

72

አዲስ አበባ ፣መጋቢት 11/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ጤና ጣቢያዎች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተለያዩ ዝግጅቶች ማድረጋቸውን አስታወቁ።

በከተማዋ የአፍንጮ በር ፣ የካ እና ጃንሜዳ ጤና ጣቢያዎች ቫይረሱን ለመከላከል ያደረጉትን ዝግጅት በማስመልከት ኢዜአ የጤና ጣቢያ ሃላፊዎቹን አነጋግሯል።

እንደ ሃላፊዎቹ ገለፃ ቫይረሱን ለመከላከል በጤና ጣቢያ ደረጃ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ስራውን በማከናወን ላይ ነው።

ታካሚዎች ወደ ጤና ጣቢያ ቅጥረ ግቢ በሚገቡበት ጊዜ እጅ ከመታጠብ ጀምሮ የሙቀት ልኬትም እየተደረገላቸው ይገኛል።

የበሽታውን ምልክት የሚያሳይ ታማሚ ከመጣም ለብቻው የሚስተናገድበት ክፍል ዝግጁ ተደርጓል ተብሏል።

የጤና ጣቢያ ሰራተኞች ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ የአፍ መሸፈኛ ማስክ እና የእጅ ጓንት እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች እየቀረቡ መሆኑን ሀላፊዎቹ ገልጸዋል። 

አሁን ላይ ከመንግስት ለቫይረሱ መከላከል ተብሎ ለጤና ጣቢያዎቹ የተሰጠ ግብዓት ባይኖርም ከዚህ ቀደም ከነበረው ክምችት እየተጠቀሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ በጤና ጣቢያዎች ይህን በሽታ ለመከላከል የሚውሉ የተለያዩ ግብዓቶች ችግር እንደሌለም ያነጋገርናቸው ጤና ጣቢያ ሃላፊዎች ገልጸውልናል።

የቫይረሱ ስርጭት እየተባባሰ የሚሄድ ከሆነ ግን እጥረት እንዳያጋጥም የሚመለከተው አካል ከወዲሁ እንዲያስብበት አሳስበዋል።

በዓለማችን በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር አሁን ላይ 250 ሺህ የደረሰ ሲሆን ከ10 ሺህ በላይ ሰዎችም ለሞት ተዳርገዋል።

በኢትዮጵያም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 9 መድረሱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም