የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮሮናን ለመከላከል ቅድመ ጥንቃቄ እያደረገ ነው

95

ሀዋሳ ፣ መጋቢት 11/2012 (ኢዜአ) የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።

በተለይ ተማሪዎች ንፅህናቸውን የሚጠብቁባቸውን ቁሳቁሶችን በማሟላት ወደ ግቢ መግቢያ በሮች፣ የመመገቢያ አዳራሾችና ሌሎች አካባቢዎች ላይ የእጅ መታጠቢዎች ማዘጋጀት ከቅድመ ጥንቃቄዎቹ መካከል ይገኙበታል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የውጭ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አርማዬ አሰፋ እንደገለፁት ተማሪዎች ስለ ቫይረሱ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ተቋሙ ባለው ማህበራዊ ሚዲያ አማካይነት መረጃዎች እንዲደርሱ እየተደረገ ነው።

ከተለያዩ ክባባት በጎ ፍቃደኛ ተማሪዎችን በመመልመልም በባለሙያዎች ሥልጠና ወስደው ለሌሎች የማሳወቅና የመከላከል ሥራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል።

ተማሪዎች በየማደሪያቸው ቢሆን የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲቀጥል መምህራን የኢንተርኔት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የፅሁፍ ሰነዶች ልከውላቸዋል፡፡

በቤተ መጻሕፍት ውስጥ የሚፈጠረውን መጨናነቅ ለመቀነስም ከወትሮው በተለየ መልኩ የንባብ ሰዓት መራዘሙንም ዳይሬክተሯ አብራርተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ቤተልሔም አዳሙ በበኩሏ "ማናችንም ብንሆን በቫይረሱ የምንያዝበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል " ብላለች።

በክባባቸው አማካኝነት በግቢው ውስጥ የኮሮናን ሻይረስ ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ በበጎ ፈቃደኝነት እየሰራች መሆኗን ተናግራለች።

"ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጋር በመሆን ራሳችንን ከቫይረሱ የመጠበቅና ሌሎችንም ስለ በሽታው ስርጭት የማስተማር ተግባራትን እያከናወንን እንገኛለን" ስትል ገልጻለች።

ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሄድ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ይበልጥ ለቫይረሱ ተጋላጭነታቸው እንደሚሰፋ ገልፃ ባሉበት ሆነው ማድረግ ያለባቸውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባም መልዕክታቸው አስተላልፋለች።

"ዩኒቨርሲቲው ንፅህናችንን የምንጠብቅባቸው አስፈላጊ ቁሳቁሶችና ሌሎች አቅርቦቶችን ለማሟላት ጥረት እያደረገ ነው" ያለው ደግሞ ሌላው በጎ ፍቃደኛ የአምስተኛ ዓመት ኤሌክትሮ መካኒካል ምህንድስና ተማሪ ዘካርያስ ምህረቱ ነው።

ተማሪዎች ስለ ቫይረሱ ስርጭት ሁኔታ ከተለያዩ ሚዲያዎች መረጃዎች ሊደርሷቸው እንደሚችሉ ጠቁሞ በራስ ላይ ብዥታን ከመፍጠር ትክክለኛ መረጃ የሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙሃን  በመምረጥ መጠቀም እንደሚገባቸውም ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም