ሃሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል የኮሮናቫይረስ የቅድመ ልየታ ጀመረ

119

አዲስ አበባ፣መጋቢት 10/2012 (ኢዜአ) ሃሎሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የልየታ ስራ መጀመሩን አስታወቀ።

ጤና ሚኒስቴር የኮሮናቫይረስ ቅድመ ልየታ በማድረግ ሂደት የግል የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲሳተፉ ጥሪ ማስተላለፉም ይታወሳል።

በግል የህክምና አገልግሎት የሚሰጠው ሃሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል የኮሮናቫይረስ

የልየታ ስራው በሆስፒታሉ መግቢያ በር ላይ እየተከናወነ መሆኑን መመልከት ተችሏል።

ሆስፒታሉ በቅድመ ልየታ ስራ የኮሮናቫይረስ ምልክት ያሳዩ ስድስት ሰዎችን በማግኘት ለመንግስት ሪፖርት አድርጎ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ማድረጉን በመግለጫው አስታውቋል።

ሆስፒታሉ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከመንግስት ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደሆነ የሆስፒታሉ ባለቤት ፕሮፌሰር ጌታቸው አደራዬ ገልፀዋል።

''መንግስት ህብረተሰቡ በኮሮናቫይረስ እንዳይጠቃ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው'' ያሉት ፕሮፈሰር ጌታቸው፤ ይህን ተግባር  ሃሌሉያ ሆስፒታል ከመንግስት ጎን በመሆን  እንደሚደግፍ ተናግረዋል ።

የመገናኛ ብዙሃን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲወጡ ፕሮፈሰር ጌታቸው  ጥሪ አቅርበዋል።

ሃሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል ከመንግስት ጋር አብሮ ለመስራት እንዲረዳው 15 አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ቃለአብ ደረጀ ገልጸዋል።

ለ400 የሆስፒታሉ ሰራተኞች ስለ ኮሮናቫይረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።

ነዋሪዎች በሆስፒታሉ ነፃ የኮሮናቫይረስ የቅድመ ልየታ ምርመራ ማድረግ እንደሚችሉም ዶክተር ቃልአብ አስታውቀዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚያስችል መልኩ ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር እየሰራ እንደሆነም ሆስፒታሉ አስታውቋል።

የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የግል የህክምና ተቋማት የኮሮናቫይረስ ለመከላከል ከጤና ሚኒስቴር  ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

በዚህም መሰረት ሃሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል የሙቀት ልየታ እያከናዎነ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሆስፒታሉ በመንግስት በኩል የለይቶ ማቆያ ክፍል እጥረት ካለ ለመተባበር ቃል መግባቱን ዶክተር ተገኔ አክለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም