የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

130

አዲስ አበባ መጋቢት 10/2012 (ኢዜ አ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።

ባንኩ አሁን ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ በቀጣይ ሁኔታዎችን እየገመገመ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል። 


የገንዘብ ድጋፉን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ለጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ               ሰሐርላ አብዱላሂ  አስረክበዋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ''በሽታው በቀላሉ በንክኪና ትንፋሽ የሚተላለፍ በመሆኑ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በትብብር መስራት ያስፈልጋል'' ብለዋል።

ባንኩ ከ23 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችና ከ62 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉትና የአገር ሀብት በመሆኑ ያለበትን ማህበራዊ ሃላፊነት በቀዳሚነት ለመወጣት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ በስጋት ደረጃ ያለ ቢሆንም የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ቀድሞ ለመከላከል እንዲያስችልና የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝም የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማደረጉን ተናግረዋል።

የባንኩ የገንዘብ ድጋፍ በአገር አቀፍ ደረጃ ወረርሽኙን ለመከላከል ለተዘጋጁት የለይቶ ማከሚያ ማዕከላት የንጽህና መጠበቂያ ሳሙናዎች፣ ጓንቶች፣ የፊት መሸፈኛ ጭምብሎች፣ ሳኒታይዘሮችና ሌሎች የተጓደሉ ግብዓቶች ማሟያ እንዲውል መሆኑንም ገልፀዋል።

በባንኩ በቅርንጫፎች ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ሰራተኞችና ተጠቃሚ ደንበኞች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን እንዲቀንሱ ለማስቻል የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ተሟልቶ ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል።

ደንበኞች የባንክ አገልግሎቶችን በዲጂታል ቻናሎች፣ በሞባይል፣ በኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ሲቢኢ ብርና በኤቲኤም እንዲገለገሉ ባንኩ እንደሚያበረታታም አቶ አቤ ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሐርላ አብዱላሂ በበኩላቸው ''በሽታው ዘር፣ ቀለምና ሀይማኖት የማይለይ በመሆኑ ሁሉም በጋራ ለመከላከል ርብርብ ማድረግ አለበት'' ብለዋል።

ህብረተሰቡ የሰላምታ ባህሉን ከንክኪ የፀዳ እንዲያደርግ ገልፀው፤ በርካታ ሰው በሚሰበሰብበት ስፍራም ርቀቱን እንዲጠብቅ መክረዋል።

በሽታው ከ80 በመቶ በላይ የመዳን እድሉ ሰፊ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሱን ከበሽታው እንዲከላከል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጀመረውን ማህበራዊ ሀላፊነት የመወጣት ድጋፍ ሌሎች ተቋማትም አርያነቱን ሊከተሉት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ህብረተሰቡ በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ የሚወጡ ሀሰተኛና ከእውነት የራቁ መረጃዎችን  ባለመከተል ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚወጡ መረጃዎችን ብቻ እንዲከታተል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም