በቤንች ማጂ ዞን የቡና ልማትን ለማስፋፋት የችግኝ ተከላ እየተካሄደ ነው

82
ሚዛን ሰኔ 22/2010 በቤንች ማጂ ዞን የቡና ልማትን ለማስፋፋት ከ27 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ተዘጋጅቶ የተከላ ሰራው እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የዞኑ ቡና ፣ሻይና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት  እንዳለው የቡና ችግኙ በስግሰጋና በአዲስ መልክ የሚተከል ነው፡፡ ከመጋቢት ወር 2010ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ከ11ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ መተከሉንና ቀሪው እስከሐምሌ ወር መጨረሻ እንደሚከናወን  በጽህፈት ቤቱ የቡና ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ምስራቅ ከበደ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ አጠቃላይ የቡና ችግኙ የሚለማው በ14ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በዞኑ የቡና ልማት በየዓመቱ እየተስፋፋ መሆኑን አመልክተው አምና ከተተከለው ሃያ አራት ሚሊየን የቡና ችግኝ ውስጥ አስራ ዘጠኝ ሚሊየኑ መጽደቁን ገልጸዋል፡፡ ዘንድሮ የሚተከለው የቡና ችግኝ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር ብልጫ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡ "ከ2005 ዓ.ም ወዲህ የተሻሻሉና ምርታማ የሆኑ የቡና ዝርያዎችን ከጂማ ግብርና ምርምር እንዲሁም ከቴፒ ብሔራዊ የቡና ምርምር ማዕከላት በማስመጣት ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ነው" ብለዋል፡፡ በዞኑ በቡና ተክል የተሸፈነው መሬት አሁን ላይ ከ138ሺህ ሄክታር በላይ መድረሱን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ 119ሺህ ሄክታሩ በአርሶ አደር ቀሪው ደግሞ በባለሀብቶች የለማ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አቶ ምስራቅ እንዳሉት ዘንድሮ የሚተከለው የቡና ችግኝ የዞኑን ሽፋን ወደ 152ሺህ ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል፤ ከ174ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በቡና ልማቱ እየተሳተፉ ነው፡፡ በሰሜን ቤንች ወረዳ የጋቅን ቀበሌ አርሶ አደር አቶ ጴጥሮስ ዘካርያስ በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ 5ሺህ የቡና ችግኝ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ የቡና ችግኝ ከማዘጋጀት ጀምሮ ባለሙያዎች በቅርበት ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸውም ገልጸዋል፡፡ ከወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ሁለት መቶ  የተሻሻለ  የቡና ዝርያ  ተሰጥቷቸው መትከላቸውን የተናገሩት ደግሞ በደቡብ ቤንች ወረዳ የማሽንባይ ቀበሌ አርሶ አደር አቶ ትዕዛዙ ባይክል ናቸው፡፡ ያላቸውን ሁለት ሄክታር የቡና ማሳ በመንከባከብ ከልማቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም