የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ዋና ጸሐፊ ቃለ-መሐላ ፈፀሙ

72

 አዲስ አበባ መጋቢት 10/2012 (ኢዜ አ) ለአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ዋና ጸሐፊ የተሾሙት ዋምኬሌ ሜኔ በአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት ቃለ-መሐላ ፈፀሙ።

ለተቋሙ  የመጀመሪያው ዋና ጸሐፊ በሆኑት ዋምኬሌ ሜኔ ቃለ-መሐላ በአለሲመታቸው  የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማትን ጨምሮ ሌሎች የኮሚሽኑ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የ42 ዓመቱ ዋምኬሌ ሜሌ ደቡብ አፍሪካዊ ዲፕሎማት ሲሆኑ በንግድ ዲፕሎማሲ፣ የመንግስት ለመንግስት የንግድ ግንኙነት ስራዎች፣ በኢንቨስትመንት እንዲሁም የኢንቨስትመንት አለመግባባቶችን በመዳኘት የዳበረ  ክህሎት እንዳላቸው ተገልጿል።

በባንክ ህግና የፋይናንስ ቁጥጥር ኤልኤልኤም እንዲሁም በአለምአቀፍ ጥናትና ዲፕሎማሲ ኤምኤ ያላቸው ዋምኬሌ ሜሜ በንግድ ቀጣናው ምስረታ ሂደት አገራቸውን ወክለው ሲሳተፉ የቆዩ ናቸው።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና በአባል አገሮች መካከል ያለውን ታሪፍ በመቀነስ፣ ንግድን በማሻሻል፣ በድንበር አካባቢ ያለውን የንግድ እንቅፋት በመቀነስና ግዙፍ የጋራ የንግድ ቀጣና በመመስረት ለአህጉሩ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት የተቀረጸውና ለፊርማ ክፍት የተደረገው በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም ርዋንዳ ኪጋሊ ላይ ነበር።



የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም