ዶ/ር ካትሪን ሀምሊን ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

259

መጋቢት 10/2012 (ኢዜአ) የፌስቱላ ሆስፒታል መስራች ዶ/ር ካትሪን ሀምሊን በ96 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዶ/ር ካትሪን ሐምሊን ሕልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካትሪን ሐምሊን ከ60 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ክብራቸው የተነጠቀባቸውን በሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ዳግም ቀና ብለው እንዲራመዱ ለፍተዋል ብለዋል።

“ኢትዮጵያ እኒህን ብርቅዬ ጌጥ አጥታለች” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚወዷቸው ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጆቻቸው እና የሥራ ባልደረቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።

ዶክተር ካትሪን በትውልድ አውስትራሊያዊ ቢሆኑም ለኢትዮጵያ ባደረጉት ውለታ ከስምንት አመታት በፊት የክብር ዜግነት ተሰጥቷቸዋል፡፡

አውስትራሊያቷ ዶክተር ኤሊኖር ካትሪን ሐምሊን ወደ ኢትዮያ መጥተው የፌስቱላ ሆስፒታልን ከኒውዚላንዳዊው ባለቤታቸው ዶክተር ሬጂናልድ ሐምሊን ጋር መስርተው ከ60 ዓመት በላይ አገልግለዋል።

በጽንስና ማህጸን ሙያቸው በፌስቱላ ችግር የሚሰቃዩ በርካታ ሴቶች ፈውስ አግኝተው ጤናማ ኑሮ እንዲገፉ አስችለዋል።

እ.አ.አ ጥር 24 ቀን 1924 የተወለዱት ዶክተር ካትሪን ሐምሊን በሆስፒታሉ ከ60 ዓመት በላይ አገልግሎት ሰጥተዋል።

በ96 ዓመታቸው ትናንት ህልፈተ ህይወታቸው የተሰማው ዶክተር ካትሪን ሐምሊን በዓለም ላይ ብቸኛ በሆነው ሐምሊን የፌስቱላ ሆስፒታል የፌስቱላ ችግር ሰለባ የሆኑ ችግረኛ ሴቶች በነጻ ህክምና ሲያገኙ መቆየታቸው ይታወቃል።

የማህጸን ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ካትሪን ሀምሊን በኢትዮጵያ ከ60 ሺህ በላይ በፌስቱላ የተጠቁ ሴቶችን ከስነልቦናዊ እና አካላዊ ቁስለት ለማዳን ችለዋል።

ዶክተር ካትሪን የፌስቱላ ቀዶ ህክምና በመስጠትና የተለያዩ የህክምና መስጫ ሙያዊ ስልቶችን በማስተዋወቅ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የቀዳሚነት ዕውቅና አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም