የአክሱም ሥልጣኔን የሚያመላክት ተጨማሪ ቅርስ በቁፋሮ ተገኘ

105

መቀሌ መጋቢት 9 / 2012 (ኢዜአ) የአክሱም ጥንታዊ ሥልጣኔን የሚያመላክቱ ወጥ የሆኑ ምሰሶዎች ፖላንዳውያንና ኢትዮጵያውያን የሥነ ጥንት ተመራማሪዎች በመቀናጀት ባካሔዱት ቁፋሮ መገኘቱን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

በሥነ ጥናት ተመራማሪዎች በቁፋሮ የተገኙት ስድስት ጥንታዊ የቤት ምሰሶዎች፣ ስብርባሪ ሸክላ፣ ፍርሥራሽ ሕንፃና በግዕዝ ቋንቋ የተጻፈባቸው ድንጋዮች ናቸው ተብሏል።

ቅርሶቹ የተገኙት በትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ሳዕስዕ ጻእዳ አምባ ወረዳ ልዩ ሥሙ ደብረ ገርግስ በተባለ ቦታ በተካሄደው ሣይንሳዊ የሥነ ጥናት ቁፋሮ  ነው።

በትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሥነ ጥንት ተመራማሪና የምርምር ቡድኑ አባል አቶ ጉዑሽ ፀሀየ ለኢዜአ እንደገለጹት ጥንታዊ ቅርሶቹ ከሰባተኛ እስከ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን የነበረውን የአክሱም ሥልጣኔ የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።

በቁፈሮ የተገኙ ምሰሶዎች ከአንድ ሜትር ተኩል እስከ አራት ሜትር ቁመት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ተመራማሪዎቹ በ72 ስኩየር ሜትር ስፋት ባለው መሬት ላይ ባካሄዱት ሣይንሳዊ ቁፋሮ የሰዎችና የእንስሳት ሥዕል ጭምር መገኘታቸውን ተናግረዋል።

በቁፋሮው ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ፣ ከቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣንና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉን የምርምር ቡድኑ አባል ገልጸዋል።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የአርኪኦሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ክብሮም ከበደ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው በፖላንድ ከሚገኘው ዋርሳው ዩኒቨርስቲ ጋር በመጻጻፍ ተመራማሪዎቹ በኢትዮጵያ ለመሥራት ፍቃደኛ እንዲሆኑ አድርጓል።

ተመራማሪዎቹ ባለፈው ዓመት የቦታ መረጣና ሌሎች ሕጋዊ ሂደቶችን አጠናቀው በቅርቡ የመጀመሪያ ደረጃ ሣይንሳዊ ቁፋሮ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ተመራማሪዎቹ በቀጣይ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በርካታ ጉድጓዶች ለመቆፈር ዕቅድ ተይዟል።

በቁፋሮው ሌሎች ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ሊገልጹ የሚችሉ ቅርሶች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሥነ ጥንት ተመራማሪው መምህር ክብሮም ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄዱ የሥነ ጥንት ምርምሮች ቅድመ አክሱም የነበሩ ቤተ ሰማዕትና ማይአድራሻ የተባሉ ጥንታዊ ፍርሥራሽ ከተሞች በቁፋሮ መገኘታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም