"የፈነዳው ቦምብ የኢትዮጵያውያንን የለውጥ ስሜት አይገታውም" - አቶ ለማ መገርሳ

99
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2010 ባለፈው ሳምንት በመስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፈኛ ላይ የተፈጸመው የቦንብ ጥቃት "በዜጎች ላይ የሄይወትና አካላዊ ጉዳት ቢያደርስም የሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን የለውጥ ፍላጎት ግን ሊገታው አይችልም" ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ተናገሩ። ፕሬዚዳንቱ ዛሬ ማምሻውን በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸው በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው የሚገኙትን የአደጋው ሰለባዎች ጎብኝተዋል። አቶ ለማ ታካሚዎቹን ከጠየቁ በኋላ በሰጡት አስተያየት "ክስተቱ እጅግ የሚያሳዝንና ለጋ ወጣቶችን ለአደጋ የዳረገ ሰይጣናዊ ተግባር ነው" ብለዋል። ለመሪው መልካም ምኞትን ለመግለፅ፣ አገሪቱ በአድገት ጎዳና እንድትራመድ ያለውን ድጋፍ ለማሳየት በወጣ ንፁሃን ህዝብ ላይ እንዲህ ዓይነት ተግባር በራሳችን ወገኖች አማካኝነት መፈፀሙ እጅግ የሚያሳዝን ነው ሲሉም ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ለማ እንዳሉት የተፈጠረው ክስተት በመቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የሚደገፈውን የለውጥ ሂደት ሊገታው አይችልም። ለውጥ ለማምጣት ዋጋ መክፈል ያስፈልጋል ያሉት አቶ ለማ መላው ዜጋ ለውጥ የግድ መሆኑን በመረዳት የተሻለች ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን አሁን ለተጀመረው ለውጥ ስኬታማነት መትጋትና መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል። የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለአደጋው ሰለባዎች እየሰጠ ላለው እርዳታም ምስጋናቸውን ለግሰዋል። የሆስፒታሉ ክልኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ዶክተር ይርጉ ገብረህይወት በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ እስካሁን በተደረገው የህክምና እርዳታ አብዛኛው ታካሚ ህክምና አግኝቶ ወደ ቤቱ ተመልሷል። አሁንም በሆስፒታሉ የሚገኙ ታካሚዎች ከጥቂቶቹ በስተቀር ህክምናቸውን ጨርሰው በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል። ሆስፒታሉ ሰሞኑን በአሶሳ በተፈጠረው ሁከት የተጎዱ ዜጎችን ለማከም አምስት አባላት ያሉት የህክምና ባለሙያዎች ቡድን ወደ ስፍራው መላኩንም ዶክተር ይርጉ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም