የኦሮሚያ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ

66

አዲስ አበባ መጋቢት 9/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የኮሮናን ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል የለይቶ ማቆያና ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረጋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ። 

የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለኢዜአ እንዳስታወቁት እስካሁን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች 7 የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል።

የለይቶ ማቆያ ስፍራዎቹ በአዳማ፣ ነቀምቴ፣ ሻሸመኔ፣ ጅማ፣ ቢሾፍቱ፣ ፊንፊኔ እና ሞያሌ የሚገኙ መሆናቸውንም  ተናግረዋል።   

በክልሉ በቫይረሱ የተያዘ ሰው ከተገኘ በአዳማና ቢሾፍቱ የህክምና መስጫ ማእከላት መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የለይቶ ማቆያ ክፍሎች እንዲዘጋጁ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

የኮረና ቫይረስን ለመከላከል በክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የገለጹት አቶ ጌታቸው ቫይረሱ ቢከሰት እንኳ ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች ዝግጁ ናቸው ብለዋል።   

ይህንኑ ጉዳይ የሚከታተል በክልሉ ምክትል ፕሬዘዳንት የሚመራ 5 የቴክኒክ ኮሚቴ መቋቋሙንም ነው የገለጹት።

ኮሙቴውም ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በበላይነት የሚመራ ይሆናልም ብለዋል፡፡  

በምርቶች ላይ ያለ አግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን ለመከላከል ይህን የሚከታተል ኮሚቴ መቋቋሙንም አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ዛሬ በሰጠው መግልጫ በሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 200 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም