የሰመራ - ሎግያ ነዋሪዎች ለህዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ

53

ሰመራ  መጋቢት 9ቀን 2012  (ኢዜአ) በአፋር ክልል የሰመራ - ሎግያ ነዋሪዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን የገንዘብ ድጋፍ አጠናክረው አንደሚቀጥሉበት ገለፁ ። 

በክልሉ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እንደገለፀው ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች 10 ሚሊዮን ብር ለመሰብስብ  እየተሰራ ነው ።

የሎግያ ከተማ ነዋሪ ወጣት አብዱ ከቢር እንደተናገረው ባለፉት አመታት ለህዳሴ ግድቡ ቦንድ በመግዛት የዜግነት ግዴታቸውን ሲወጣ ቆይቷል ።

መንግስት በግድቡ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚያደርገን አቋም መያዙን ተገቢ ቢሆንም በግብፅ በኩል የተሰጠው ምለሽ  ህጋዊነት የሌለው በመሆኑ በእልህ የጀመርነውን ለመጨረስ መነሳሳት ፈጥሮልናል ብሏል ።

ከተሰማራበት የግል ስራ ከሚያገኟት ውስን ገቢ ቦንድ በመግዛት ለህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ የራሱን ገንቢ አስተዋጽኦ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አስረድቷል ።

የሰመራ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አስያ ኡስማን በበኩላቸው ልማት በመንግሰት ውስን በጀት ብቻ ሳይሆን በህበረተሰቡን ንቁ ተሳትፎ የሚረጋገጥ በመሆኑ የህዳሴ ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፌን አጠናክሬ አቀጥላለሁ ብለዋል ።

በዚህ አመት ለ4ኛ ጊዜ ከወርሃዊ ደመወዛቸው በግማሹ ቦንድ ለመግዛት መወሰናቸውን አስረድተዋል ።

በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት የሎግያ ከተማ ነዋሪ አቶ አብዱልአዚዝ መሃመድ በሰጡት አስተያየት ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ እስከ አሁን በቦንድ ግዥና በስጦታ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን  ገልፀዋል ።

የግድቡ ግንባታ በወሳኝ ምእራፍ ላይ የሚገኝ በመሆኑ በቀጣይም አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ግዴታ እንደሚወጡ ተናግረዋል ።

የአፋር ክልል የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ድጋፍ ማስተባባሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኡስማን ጠሃ እንዳሉት ባለፉት አመታት በክልሉ 138 ሚሊዮን ብር በቦንድ ግዥና በድጋፍ አርብቶ አደሩን ጨምሮ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተሰበሰበ መሆኑን አስረድተዋል ።

ይህም በ5 አመት ውስጥ ለመሰብሰብ ከታቀደው አንጻር ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አብራርተዋል ።

ጽህፈት ቤቱ በዚህ የበጀት አመትም  10 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

በየደረጃው ከሚገኙ የዞንና ወረዳ አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን የህዝብ ንቅናቄ ስራ እየተከናወነ ሲሆን እስከ ቀበሌ ድረስ የሚወርድ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት እንደሚዘጋጅ ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም