የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ተማሪዎች ሳይዘናጉ ጊዜያቸውን በጥናት ሊያሳልፉ ይገባል አለ

64

ባህርዳር( ኢዜአ )መጋቢት 9/2012 ፡- የኮረና ቫይረስን ለመከላከል ለጊዜው ትምህርት ቤቶች ቢዘጉም ይህንን ለማካካስ ተማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ሳይዘናጉ በጥናት እንዲያሳልፉ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አሳሰበ።
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮረና ቫይረስ ተስፋፍቶ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል መንግስት ትምህርት ቤቶች ለ15 ቀናት ተዘግተው እንዲቆዩ መወሰኑን አስታውሰዋል።

ይህን  ተከትሎ  በክልሉ የሚገኙ 10 የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆችን ጨምሮ ሁሉም የአንደኛና ሁለተኛ  ደረጃ ትምህርት ቤቶች  እንዲዘጉ ተደርጓል።

በተለይ ተማሪዎች መጪው ጊዜ ክልላዊና ሀገር አቀፍ ብሄራዊ ፈተና የሚወስዱበት በመሆኑ የተማሩትን ትምህርት በመከለስና በማጥናት ጊዜያቸውን ለፈተና ዝግጅት ማዋል ይጠበቅባቸዋል።

ወላጆችም ይህንኑ ተገንዝበው ልጆቻቸውን ከኮረና ቫይረስ ከሚያጋልጡ ነገሮች በማራቅ ጊዜያቸውን በጥናትና ንባብ እንዲያሳልፉ ተገቢውን ዕገዛ  ሊያደርጉላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

በባህርዳር የጣና ኃይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሙጨ ባዘዘው በበኩላቸው ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገለፀው አግባብ የመማር ማስተማር ስራ መቆሙን ገልጸዋል።

ተማሪዎችም የተማሩትን ትምህርት በመከለስና  ወርክ ሽትን( የተሰጣቸውን የቤት ስራ ) ጊዜ ሰጥተው በመስራት ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ምክረ ሃሳብ በመስጠት እንደሸኟቸው ተናግረዋል።

ተማሪዎችም ለበሽታው ከሚያጋልጡ ነገሮች ራሳቸውን በማራቅ መምህራኖቻቸው በሰጧቸው አቅጣጫ መሰረት ሙሉ ጊዜያቸው ለጥናት ሊያውሉት እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

"መንግስት የኮሮና ቫይረስ እንዳይዛመት ትምህርት ቤቶችን በጊዜያዊነት መዝጋቱ ተገቢ ነው" ያለው ደግሞ የዚሁ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ተመስገን ንጉሴ ነው።

የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ብሄራዊ ፈተና እየተቃረበ በመሆኑም በማጥናት ጊዜውን ለማሳለፍ እንደተዘጋጀም ተናግሯል።

ቤተሰቦቹ ለፈተናው ያግዛሉ ያሏቸውን የተለያዩ መጽሐፎች ቀደም ሲል ገዝተው በማቅረባቸው ለውጤት የሚያበቃው ጥናት እንደሚያደርግም ገልጿል።

በክልሉ ከ4 ሚሊዮን የሚበልጡ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በትምህርት ላይ እንደነበሩ ከትምህርት ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም