የአንበጣ መንጋውን በባህላዊ መንገድ መከላከል ተችሏል

59

ደብረ ማርቆስ፤  9/07/2012( ኢዜአ) በምስራቅ ጎጃም ዞን ተከስቶ የነበረውን የአንበጣ መንጋ በባህላዊ የመከላከል ዘዴ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። 

የመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አበባው እንየው ለኢዜአ እንደተናገሩት የአምበጣ መንጋው ከየካቲት ወር መግቢያ ጀምሮ  በ15 ወረዳዎች በሚገኙ 130 ቀበሌዎች ተከስቶ ነበር ።

የአንበጣ መንጋው በአንዳንድ ወረዳዎች በመስኖ እየለሙ ባሉት ማሳዎች ለማረፍ ሙከራዎች ያደረገ ቢሆንም ማህበረሰቡ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀምና ተማሪዎችን በማሳተፍ ጉዳት ሳያደርስ መከላከል መቻሉን ጠቅሰዋል።

የአንበጣ መንጋውን ጥሩንባ በመንፋት፣ ባረፈበት አካባቢ የከብት መንጋ መንዳት፣ ጅራፍ ማጮህና የመሳሰሉትን ድምጾች በማሰማት በባህላዊ መንገድ የመከላከል ስራ ተከናውኖ ውጤታማ  መሆኑ ተገልጿል ።

አንበጣው ተረጋግቶ ባረፈበት እንዳይቆይ በማድረግ በተደረገው ከፍተኛ ጥረት ከመጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት እንደተቻለ ባለሙያው ተናግረዋል ።

ማህበረሰቡ የአንበጣ መንጋውን ካባረረ በኋላም እንቁላል ሊጥልባቸው ይችላል ተብሎ በተጠረጠሩ አሸዋማ አካባቢዎች አሸዋውን በመበተን እንዳይራባ የመከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

መንጋው ዳግም እንዳይከሰትና ከተከሰተም ፈጥኖ ማባረር እንዲቻልም በስራ ላይ የነበረው ግብረ ሃይል ሳይዘናጋ የክትትልና የቁጥጥር ተግባራት እየተሰሩ ናቸው ብለዋል።

የእነብሴ ሳርምድር ወረዳ የተንታ ቀበሌ ነዋሪ አር ሶአደር ይስማው አለነ በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ የአካባቢው አርሶ አደር ተደራጅቶ ማባረር ችሏል።

የአካባቢው አርሶ አደር ሌትና ቀን ድምጽ በማሰማት ለማባረር ባደረገው ጥረት አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ አካባቢውን ለቆ መሄዱ ተገልጿል።

በአካባቢው ታይቶ በማይታወቅ መንገድ በመውረር 10 ቀናት የቆየው የአንበጣው መንጋ አስደንግጧቸው እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የጎንቻ ወረዳ ሰላምጌ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተፈራ ይግዛው ናቸው።

መጀመሪያ አካባቢ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር አስቸግሮ እንደነበር አስታውሰው ህፃናትን ጨምሮ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ በተደረገ ርብርብ  መንጋውን በማባረር ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም