የኮሮና ቫይረስን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ... የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮና ቫይረስን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ... የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ
ሶደ መጋቢት 9/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጉንና ለማከሚያና ማቆያ የሚሆን ማዕከል ማዘጋጀቱን የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡
የወላይታ ዞን ከፍተኛ የንግድ እንቀስቃሴና የቱሪስት ፍሰት ያለበት አካባቢ በመሆኑ፤ የኮሮና ቫይረስ እንዳይከሰት የቅድመ መከላከል ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሣለኝ ፋንታ ገልፀዋል ።
በዞኑ በቻይናውያን የሚሰሩ ሶስት ፕሮጀክቶች መኖራቸው ጠቁመው ወደ ሃገራቸው ደርሰው ለተመለሱ ቻይናውያን ተገቢው ምርመራ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
ከቫይረሱ በቀላሉ ለመቆጣጠር እንዲያስችል ግብረ-ሃይል መቋቋሙንም አቶ ደሣለኝ ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው በአሁኑ ሰዓት ምንም ዓይነት የቫይረሱ ምልክት ያለበት ሰው አለመኖሩን ያነሱት ኃላፊው ይሄም ዋስትና ሊሆን ስለማይችል ለህብረተሰቡ የጤና ግንዛቤ ትምህርት እየተሰጠ ነው ብለዋል ።
በሽታው ቢከሰት መቆጣጠር እንዲቻል በሶዶ ከተማ ከሚገኙ ሦስት ጤና ጣቢያዎች መካከል የገነሜ ጤና ጣቢያ ሌሎች አገልግሎቶችን ለጊዜው በማቆም የኮሮና ቫይረስ ማከሚያና ማቆያ ስፍራ እንዲሆን መወሰኑን አስታውቀዋል።
የግብዓት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት በቂ ዝግጅት መደረጉንና ለመረጃ ልውውጥ እንዲያመች ነፃ የስልክ መስመር ለመዘርጋት ከቴሌኮሙኒኬሽን ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡