በወጣቶች ላይ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል የፍትህ አካላት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተጠቆመ

123
አዳማ ሰኔ 22/2010 በወጣቶች ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል የፍትህ አካላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ በአገሪቱ ህጎች፣ በወጣቶች ማህበራዊ ጉዳዮችና በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬህይወት አያሌው በመድረኩ ላይ እንዳሉት የፍትህ አካላት ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትለው በወጣቶች ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን ሊከላከሉ ይገባል። "በአሁኑ ወቅት ወጣቶች የአገሪቱ የለውጥ ጉዞ በማፋጠን በኩል አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ እየሰሩ ቢሆንም ለውጡን በአግባቡ መምራት ባለመቻሉ ህግ እየተጣሰ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ አደጋ የሚከሰትበት ሁኔታ ይስተዋላል" ብለዋል። "ችግሩን ለመፍታት በፍትህ አካላትና በወጣቶች መካከል ጤናማ ግንኙነት ሊኖር ይገባል" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በተለይ ወጣቶች በነባር የህግ ማዕቀፎች ላይ ግንዛቤ እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። የህግ ክፍተቶች ሲያጋጥሙም በረቂቅ ሰነድ ዝግጅት ላይ ወጣቶች በየደረጃው እንዲሳተፉ በማድረግ ስለመብታቸው እንዲጠይቁና ለሌላውም መብት መከበር የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ነው የጠቆሙት ። በሚኒስቴሩ የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ማቲያስ አሰፋ የወጣቶችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከማስጠበቅ አንጻር ያጋጠሙ ችግሮች ላይ አተኩሮ የተካሄደውን አገራዊ የጥናት ግኝት በመድረኩ አቅርበዋል። በጥናቱ ከተለዩ ችግሮች መካከል የወጣቱን ንቃተ ህግ ለማዳበር በፍትህና በፀጥታ አካላት የሚሰሩ ሥራዎች አናሳ መሆን አንዱ ነው። ህግን ከማስተማር ይልቅ ህጋዊ እርምጃዎችን የመውሰድ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱም እንዲሁ በጥናቱ ተለይቷል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ወጣቶችን የተመለከቱ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ህጎች፣ ስምምነቶችና ፕሮቶኮሎች ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ተግባረዊ ከማድረግ አንጻር እየተሰራ ያለው ሥራ ውሱንነት እንዳለበት በጥናት ተለይቷል። "በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተቋማትና በዩኒቨርሲቲዎች አቅራቢያ ያሉ የንግድ ተቋማትና መደብሮች የንግድ ፈቃድ አሰጣጥና ክትትል  በጥናት ላይ የተመሰረተ አለመሆኑም እንዲሁ። ህግን ከማስከበር አንፃር ትኩረት ሰጥቶ አለመስራትና ሌሎችም የተስተዋሉ ተገዳሮቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። አቶ ማቲያስ እንዳሉት ጫት ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር በወጣቱ ትውልድ ላይ እያደረሰ ያለውን ማህበራዊ ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ የለም። በወጣቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮቹን ለመከላከል የፍትህ አካላት በህገ- መንግስቱና በሰብዓዊ መብቶች፣ በወንጀለኛና የፍትሃ-ብሔር ህጎች ዙሪያ የወጣቶችን ንቃተ ሕግ ለማደባር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መስራት እንዳለባቸው ጥናቱ አመላክቷል። በወጣቶች ዙሪያ ያሉ የወንጀል መነሻዎችን በማጥናት ወንጀል የሚቀንስበትን ስልት መቀየስና የቅድመ መከላከል ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባም ነው ያመለከተው። የመድረኩ ተሳታፊዎች ጥናቱ ሰፋ ያለና ወቅታዊ መሆኑን ገልጸው በመድረኩ በአገሪቱ ወጣቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመግታት የጋራ ጥረት ማድረግ ወሳኝ እንደሆነ የተሻለ ግንዛቤ መያዛቸውን ተናግረዋል። በተለይም የፌዴራል ፖሊስ አባል የሆኑት ኮማንደር ታደሰ ተክለማርያም ጥናቱ እስካሁን ያልተዳሰሱ ችግሮችን ያወጣ መሆኑን ገልጸው ለተግባራዊነቱ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም