"ኢትዮጵያ በዓረቡ ዓለም" የጋዜጠኛው ማስታወሻ

75

በሚስባህ አወል /ኢዜአ/

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተነሳ ቁጥር በአንድ ወቅት ያነበብኳት ጽሁፍ በአዕምሮዬ ታቃጭላለች፡፡ ጥሎብኝ ሌሊት ላይ እንቅልፍ እምቢ ሲለኝ ካሉኝ መፅሃፍት አንዷን ሳብ አድርጌ ማንበብ ልማዴ ነው።

በአንዱ ሌሊት ታዲያ እንደዚሁ እንቅልፍ እምቢ ቢለኝ እጄን ወደ መፅሃፍቶቼ ሰደድኩ “በሕይወቴ ሂደት ዙሪያ” የሚለው የሀጅ በሽር ዳውድ መጽሀፍ በእጄ ገባ።

ንባብን እንቅልፌን ለማምጣት ከምጠቀምበት ዘዴ አንዱ ቢሆንም አንዳንዴ በንባቡ ጠለቅ ብዬ እሄዳለሁ አሊያም እንቅልፌ ራሱ ይዞኝ ይሄዳል።

በዛን ዕለት ያነሳሁትን መፅሃፍ ላይ ላዩን ገረፍ ገረፍ እያደረኩ ሳለ ድንገት “ኢትዮጵያ በዓረቡ ዓለም” የምትለዋ ርዕስ ትኩረቴን ሳበችው።

ደራሲው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ጋዜጠኛ ሆነው በሚያገለግሉበት ወቅት የገጠማቸውን ነው ያሰፈሩት።

የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር መኮንን ሀብተወልድ የዓረቡን ዓለም ዘገባዎች ተከታትለው በመተርጎም እንዲያቀርቡ በታዘዙት መሰረት በአንድ ወቅት የገጠማቸውን ነበር እንዲህ ያሰፈሩት።

የግብጹ ፕሬዚዳንት በአገራቸው ሬዲዮ ለደጋፊዎቻቸው ከስድስት ሰዓት የበለጠ ጊዜ የወሰደ ንግግር ያደርጋሉ።

በዚህ ንግግራቸው ኢትዮጵያንና የዓባይ ግድብን የተመለከተ ዲስኩር አሰምተው ስለነበር “እንደሚከተለው ተርጉሜ ለመኮንን ሀብተወልድ አቀረብኩ” ነው ያሉት ሀጂ በሽር በመጽሀፋቸው። ትርጉሙም እንደሚከተለው ነበር።

“የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገስት ኃይለሥላሴና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የዓባይን ውሃ አግደን የግብጽን ሕዝቦች በውሃ ጥም እንጨርሳለን በማለት ጠዋት ማታ ይደነፋሉ። በመሰረቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓባይ ውሃ የመጠቀም ሙሉ መብት አለው። እኔም በዚሁ ረገድ እንፈራረም ብለው ቢጠይቁኝ አልቃወምም። ምክንቱም እነሱ ሊጠቀሙ የሚችሉት የዓባይን መጋቢ የሆኑትን ወንዞች በመገደብ ብቻ ነው። እኛ የምንጠቀመው...” እያለ ይቀጥላል።

ነገሩ አግራሞትን ጫረብኝ። መፅሃፉ የታተመው በመጋቢት 2003 ዓ.ም ቢሆንም ታሪኩ ከ50 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። ለካ የአባይ ግድብ የታቀደው ከዘመናት በፊት ነው ብዬ አሰብኩና ወደ ንባቤ ተመለስኩ። ጀማል አብዱልናስር ንግግራቸውን ቀጥለዋል፤ ሀጂም መተርጎማቸውን።

“አላህ ኢትዮጵያን ሲፈጥር ከቀይ ባህርና ከኤርትራ ጀምሮ እስከ ኬንያ ድረስ እጅግ ወደ ላይ ከፍታ ባለው ጋራና ተራራ ላይ ነው። እኛን ደግሞ በኢትዮጵያ ምዕራብ በኩል እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ሜዳ ላይ ነው። በዚህ ከፍተኛ ተራራ ገፅ ላይ ዝናብ ሲጥል ጎርፍ የኢትዮጵያን አፈርና ደለል ይዞ ወደእኛ መምጣቱ አይቀርም። ታዲያ ይህን አላህ የፈጠረውን የታላቁን ዓባይ ወንዝ ፍሰት ለመለወጥ ወይም ለመገደብ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ታላላቅ ነን የሚሉት እነ አሜሪካ ሁሉ ቢተባበሩ ሊገድቡት አይችሉም።”

መፅሀፉ እየመሰጠኝ መጣ፤ የጀመርኩት እንቅልፌን እንዲያመጣልኝ ሆኖ ሳለ ይልቁንም አንቅቶኝ ቁጭ አለ።

ፕሬዚዳንት ጀማል አብዱልናስር ንግግራቸውን ቀጥለዋል።

“እኛ ለመጠጥ የምንጠቀመው ከዓመት ዓመት ሳይቋረጥ ከኡጋንዳ የሚመጣን ውሃ ነው፤ ከኢትዮጵያ የሚመጣውን የምንጠቀመው በዚያ ከፍተኛ ተራራ ላይ ዝናብ በኃይል ሲጥል ጎርፍ ተሸክሞ የሚያመጣውን አፈርና ደለል ነው። እኛ ወደፊት በዚህ ውሃ ይበልጥ ለመጠቀም የምንችለው ወደእኛ መሬት ላይ መግባት በሚጀምርበት አስዋን ከተማ ላይ ታላቅ ግድብ ሰርተን መሆን አለበት።”

ለካ የዛኔ አስዋን አልተገነባም ነበር አልኩ በውስጤ!! ጀማል አብዱልናስር ንግግራቸውን፤ ታሪክ ጸሐፊው ሀጂ በሽርም ትርጉማቸውን፤ እኔም ማንበቤን ቀጥለናል።

“በዚህ መሰረት እኛንና ኢትዮጵያን የሚያጣላን ምንም ነገር የለም። ኃይለሥላሴ ግን ውሸታም ነው፤ ለህዝቡ አይሰራም፤ ጌቶቹ አሜሪካኖች ዓባይን እንቆጣጠራለን ብለህ አስፈራራ ይሉታል። የአሜሪካኖች ጅራት ነው። እኔም መልስ የምሰጠው ለጌቶቹ እንጂ ለጅራት መልስ አልሰጥም። ኃይለስላሴ ለህዝቡ የሚሰራ እውነተኛ ንጉስ ከሆነና እንፈራረም ቢለኝ ለሁለታችንም ህዝቦች ጥቅም ስል ምንም ሳላመነታ እስማማለሁ። እፈርማለሁ።” በማለት የተናገሩትን ንግግር ነበር ሀጂ በሽር ተርጉመው ጠዋት ለሚኒስትሩ መኮንን ሀብተወልድ እንዳቀረቡ በፅሁፋቸው የገለጹት።

ይህ ንግግር ለንጉሡ እንደደረሰ ውለው ሳያድሩ ነበር ካይሮ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተገኙት።

አፄ ኃይለስላሴና ጀማል አብዱልናስር ብጤ የሌላቸው ወዳጆች ሆኑ ይሉናል ሀጂ ምክንያቱ በውል ባይታወቅም። የአፍሪካ ኅብረትን በመመስረት አንጸባራቂ ስም ለማግኘት የሚሹት ንጉሥ ኃይለስላሴ ዲፕሎማሲዊ ስራቸውን እንዳስተካከሉ በመጠቆም።

ጀማል አብዱልናስር የአስዋንን ግድብ አስገንብቶ ለህዝቡ ይፋ ሲያደርግ የእኛ የዓባይ ግድብ ጉዳይ ግን የውሃ ሽታ ሆኖ መቅረቱን ሀጂ በሽር በመጽሀፋቸው አትተዋል።

ከላይ በቀረበው የግብፁ መሪ ንግግር ውስጥ እጅጉን ያስገረሙኝ ሁለት ፍሬነገሮች ናቸው።

በወቅቱ የኢትዮጵያ ገንዘብ የመግዛት አቅም ከፍተኛ በነበረበትና እንደ አሜሪካና እንግሊዝ ያሉ ታላላቅና ገናና አገራት ከኢትዮጵያ ጎን በቆሙበት ወቅት የግብጹ መሪ ጀማል አብዱልናስር በአደባባይ የተናገሩት ንግግር አንዱ ነው።

“የታላቁን ዓባይ ወንዝ ፍሰት ለመለወጥ ወይም ለመገደብ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ታላላቅ ነን የሚሉት እነ አሜሪካ ሁሉ ቢተባበሩ ሊገድቡት አይችሉም።” ያሉት በአዕምሮዬ ውስጥ እየተመላለሰ ያቃጭላል።

ዛሬ የኢትዮጵያ ገንዘብ የመግዛት አቅም ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ ወርዷል። ኢትዮጵያን በሕዳሴው ግድብ ላይ የሚደግፋትም ሆነ የሚረዳት አገር የለም። ግድቡ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አቅምና ገንዘብ የሚገነቡት ነው። አሜሪካም ሆነች ሌሎች የበለፀጉ አገራት ጉዳያቸው ከጥቅማቸው ጋር የተቆራኘ ሆኗልና!!

እናም ዛሬ ግድቡን መገንባት ላይ ሳይሆን በውሃ ሙሌቱ ላይ ነው ድርድሩ ስለዚህ የጀማል አብዱልናስር ንግግር ጊዜ ያለፈበት መሆኑን እዚህ ላይ ልብ በልሉልኝ።

ይሁንና ዛሬም ቢሆን በግብጽ በኩል የኢትዮጵያን ትጋትና ህልም ለማጨናገፍ የማይቆፈር ጉድጓድ እንደሌለ የሰሞኑ የአሜሪካና የዓለም ባንክ እንዲሁም የዓረብ ሊግ መግለጫዎች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው።

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የግንባታ ሥራው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለፉ ዓመታት ታሪካችንን ለመቀየርና ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ ለማምጣት አንዱ መንገድ በመሆኑ ለግድቡ ግንባታ የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር ያስፈልጋል።

የግድቡ ግንባታ ከ71 በመቶ በላይ በመድረሱ ይመስለኛል ድርድሩ ግድቡ ይገንባ አይገንባ መሆኑ ቀርቶ በውሃ አሞላሉ ላይ የሆነው። የግንባታው መሰረት በተጣለበት ጊዜ ግድቡ 63 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚይዝም ተገልጾ ነበር።

የሁለተኛው ግራሞቴ ነጥብ ደግሞ አገራት ከያዙት ፖሊሲና ጥቅም አንጻር እንዴት እንደሚገለባበጡ ያየሁበ ነው። በዚያን ወቅት አሜሪካ ለኢትዮጵያ እንዴት ወገቧን ይዛ ትከራከር እንደነበርና የዛሬ አቋሟ ምን እንደሆነ ሳስበው እንዲህ ያለው የአቋም መቀያየር ዓለም እንቅስቃሴዋ ምን ያህል ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን በግልጽ ያሳያል።

ያኔ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የወገነችበትን ሁኔታ አንዳንድ ምሁራን በነበረው የርዕዮተ ዓለም ሁኔታዎች ኢትዮጵያ ከሶሻሊስቱ ጎራ የራቀች መሆኑን ያነሳሉ። ቃኘው ሻለቃ የጦር ሰፈር፣ ኢትዮጵያ በወቅቱ ከአሜሪካ ጋር የነበራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና የተለያዩ ምክንያቶችንም ሲያቀርቡ ይደመጣል።

ወጣም ወረደ በእኔ ምልከታ ጉዳዩ በጥቅምና ጥቅም ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆኑን ነው የምረዳው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም