ሁሉም የተፋሰሱ አባል ሀገራት በአባይ የመጠቀምና የመልማት ተፈጥሯዊ መብትም እውቅናም ሊሰጠው ይገባል -- ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ

68

መጋቢት 8/2012 (ኢዜአ) የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በትላንትናው እለት ከሩዋንዳው ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ጋር በኪጋሊ ተገናኝተው በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡

ፕሬዝደንት ፓል ካጋሜ በዚህ ወቅት ባደረገት ንግግር በአባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል የሚደረገው የትብብር እንቅስቃሴ ከሁሉ በፊት ቴክኒካዊ ለሆኑ ጉዳዮች ቅድሚያ የሚሰጥና የሚደረጉ ትብብሮችም በዚህ ላይ የተመሰረቱ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡

በቴክኒካል ባለሙያዎች የሚቀርቡ ሳይንሳዊ ትንተናዎች እስከተያዙ ድረስ ውጤቱም የጋራ ፍላጎትን የሚያንጸባርቅ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ከመርህ አንጻርም በግብጽ በኩል ወንዙ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ የሚነሳውን ያህል የሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት በአባይ የመጠቀምና የመልማት ተፈጥሯዊ መብትም እውቅና ሊሰጠው ይገባል ።

የአባይ ጉዳይ የሁሉም ተፋሰስ ሀገራት ጉዳይ መሆኑን አጽንዎት ሰጥተው የተናገሩት ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ በወንዙ አጠቃቀም ዙሪያ የሚነሱ አለመግባባቶችም በአፍሪካውያን የውይይትና የድርድር መድረኮች ሊፈቱ እንደሚገባ አመልክተዋል ፡፡

ለዚህም ስኬታማነት ሀገራቸው የሚጠበቅባትን አስተዋጽዎ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ፕሬዝዳንት ካጋሜ ገልጸዋል፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ እንዲሰፍን ጠንካራ አቋም ይዛ ከተቀሩት የተፋሰሱ ሀገራት ጋር በቅርበት ስትሰራ መቆየቷን ተናግረዋል ፡፡

በተለይም የአባይ ተፋሰስ ሀገራት እ.አ.አ ከ1999 ጀምሮ ለ10 ዓመታት ገደማ ሲያደርጉት የቆዩት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ዳር እንዲደርስ የተጫወተችው ሚና ከዚህ የጸና ቁርጠኝነቷ የሚመነጭ መሆኑንም ፕሬዝዳንቷ አብራርተዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብንም መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ማለትም በሱዳንና በግብጽ በኩል የሚነሱ ስጋቶችን ለመቅረፍ እና መተማመንን ለመፍጠር የሶስትዮሽ መድረኮችን በማመቻቸት ጭምር በጎ አስተዋጽዎ መጫወቷን ጠቅሰዋል ፡፡

በዚህም ጥረት በኢትዮጵያ ፤ ሱዳንና ግብጽ መካከል እ.አ.አ በ2015 የመርህ ስምምነት (Agreement on Declaration of Principles) በካርቱም እንደተፈረመ አስታውሰዋል ፡፡

አሁንም ኢትዮጵያ በዚህ ስምምነት ላይ የሰፈሩት መርሆች ወደ ተግባር ተቀይረው የአባይ ተፋሰስ የግጭት እና የአለመግባባት ምንጭ ሳይሆን የትብብርና የጋራ ልማት ማዕከል እንዲሆን ያላትን ፍላጎት ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም